Get Mystery Box with random crypto!

ቅዳሜ ሐምሌ 23/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የተመድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽ | ኢ.ዜ.አ

ቅዳሜ ሐምሌ 23/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የተመድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዙሪያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማስረጃ ያላቸው ቡድኖችና ተቋማት ሁሉ እስከ ሐምሌ 24 ድረስ በእጃቸው ያሉ ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡለት ጥሪ አድርጓል። ማስረጃዎች በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ዓለማቀፍ ወንጀሎች፣ የጦርነት ወንጀሎችና በስደተኛ ዓለማቀፍ መብቶች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያስረዱ እንዲሆኑ እና የጥፋተኞችን ማንነት እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ያካተቱ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ጠይቋል። ማስረጃ አቅራቢዎች ማስረጃዎችን የሚያስገቡት፣ በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ድረገጽ ላይ የተቀመጠውን ቅጽ በመሙላት እንደሆነ ተገልጧል። ቅፁን እዚህ ይመልከቱ- https://www.ohchr.org/en/hr-bodies/hrc/ichre-ethiopa/call-for-submissions

2፤ በደቡብ ክልል ሀድያ ዞን፣ ሀላባ ዞን፣ ከምባታ ጠምባሮ ዞን እና የም ልዩ ወረዳ በአዲስ ክልል ሥር ባንድ ላይ ለመዋቀር በየምክር ቤቶቻቸው ዛሬ ውሳኔ መወሰናቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የጉራጌ ዞን እና ስልጤ ዞን ምክር ቤቶችም በዚሁ መዋቅር ስር ለመካተት ሊወስኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ባለፉት ሦስት ዓመታት የደቡብ ክልል አካል የነበሩት ሲዳማ ዞን እና የክልሉ ምዕራባዊ የአስተዳደር መዋቅሮች ከደቡብ ክልል በመውጣት፣ ሲዳማ ክልልን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ማቋቋማቸው ይታወሳል።

3፤ በተመሳሳይ በደቡብ ክልል የወላይታ ዞንን ጨምሮ 11 ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ከደቡብ ክልል ወጥተው አንድ አዲስ ክልል ለማቋቋም በየምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ከደቡብ ክልል ወጥተው ባንድ አዲስ ክልል ስለ ለመዋቀር የወሰኑት፣ ወላይታ ዞን፣ ጋሞ ዞን፣ ጎፋ ዞን፣ ጌዲዖ ዞን፣ ኮንሶ ዞን፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ቡርጅ ልዩ ወረዳ፣ ባስኬቶ ልዩ ወረዳ፣ አማሮ ልዩ ወረዳ፣ አሌ ልዩ ወረዳ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ናቸው። የደቡብ ክልል መንግሥት የክልልነት ጥያቄ ያነሱ የአስተዳደር መዋቅሮች ዛሬ ያሳለፉትን ውሳኔ አድንቋል።

4፤ ኢትዮ ቴሌኮም አፍሪካ ውስጥ በቴሌኮም ዘርፍ ከተሠማሩ ኩባንያዎች የባለቤትነት ድርሻ ለመግዛት የሚያስችሉትን ሥራዎች እያጠናቀቀ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለፁ ። ኩባንያው ሙዓለ ንዋይ የሚያፈስባቸውን አገራት መርጦ በቴሌኮም ዘርፋቸው ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን፣ ሆኖም ፍሬሕይወት የአገራቱን ስም ከመጥቅስ ተቆጥበዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌኮማቸውን ጠቅልሎ እንዲገዛላቸው የጠየቁ አገራት መኖራቸውንም ፍሬሕይወት ተናግረዋል። ፍሬሕይወት ለጊዜው ዕቅዳችን ድርሻ መግዛትና የሌሎችን ቴሌኮሞች ማኔጅመንት መረከብ ነው ብለዋል።

5፤ ዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ አስፈላጊ መድኻኒቶችን በሚያጓጉዝ የኪራይ ካሚዮኑ ውስጥ "ሰርዶ" በተባለ ፍተሻ ኬላ ላይ ከተገኙት ያልተፈቀዱ ጥሬ ገንዘቦችና የተለያዩ ዕቃዎች ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የካሚዮኑ ሹፌሩም ወዲያውኑ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ድርጅቱ አክሎ ገልጧል። የሹፌሩን ያልተገባ ድርጊት ያወገዘው ቀይ መስቀል፣ ክስተቱ ሰብዓዊ ዕርዳታ በማጓጓዝ ተልዕኮዬ ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ጥረት እያደረግሁ ነው ብሏል።

6፤ ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ላይ የሦስትዮሽ አስገዳጅ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ኢትዮጵያ በተናጥል የግድቡን ሦስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ለማከናወን የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደምትቃወም አስታውቃለች። ግብጽ ይህንኑ ተቃውሞዋን የገለጸችው፣ ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በላከችው አዲስ ደብዳቤ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ሦስተኛውን ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት በተያዘው ሐምሌ እና ነሐሴ ወር እንደሚያካሂድ መግለጹ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ዘንድሮ ግድቡን እንደምትሞላ ከ5 ቀናት በፊት እንዳሳወቀቻት የገለጸችው ግብጽ፣ የግድቡ የተናጥል ሙሌት ሊፈጥርብኝ የሚችለውን ተጽዕኖ ጨምሮ ብሄራዊ ደኅንነቴን ለማስጠበቅ ሁሉንም ዓይነት ርምጃዎች እወስዳለሁ ስትል በደብዳቤዋ አስጠንቅቃለች።

7፤ የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ዓለማቀፍ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ እስካሁን በ78 አገራት ከ16 ሺህ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ተገኝቷል። በሽታው ባለፉት ጥቂት ወራት በዓለም ላይ በስፋት መሰራጨት ከጀመረ ወዲህ፣ እስከ ትናንት ድረስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የሞቱት አፍሪካ ውስጥ ብቻ ነበር። ሆኖም ትናንት ከአፍሪካ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ስፔን እና ብራዚል በበሽታው የተያዙ ሰዎች እንደሞቱባቸው ሪፖርት አድርገዋል። አፍሪካ እስካሁን የበሽታው መከላከያ ክትባቶች በእጇ የሏትም።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)