Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች በሱማሊያዋ ባኮል | ኢ.ዜ.አ

ዓርብ ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች በሱማሊያዋ ባኮል ግዛት ውስጥ "አቶ" በተባለ ወረዳ ዛሬ ከአልሸባብ ታጣቂዎች ጋር በድጋሚ እንደተዋጉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የአልሸባብ ታጣቂዎች በክልሉ ልዩ ኃይል ላይ ዛሬ ጧት ሞርታሮችን በመተኮስ ውጊያውን እንደጀመሩ ዘገባዎች አመልክተዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማምሻውን ለመንግሥት ዜና አውታሮች በሰጠው መረጃ፣ ቡድኑ ትናንት ሌሊት በከፈተው አዲስ ውጊያ በድጋሚ ተመቶ መመለሱን እና ከ150 በላይ ታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግሯል።

2፤ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪው የቀድሞ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥር አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ 14 ተጨማሪ ቀናት መፍቀዱ ተገለፀ። ችሎቱ በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥሮ በታሰረው ልጃቸው እያሱ ምትኩ ላይ ደሞ 10 ቀን ፈቅዷል። ምትኩ እና ልጃቸው ችሎቱን በአካል ተከታትለዋል። ኤልሻዳይ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመመሳጠር ከኮሚሽኑ በተመዘበረ ገንዘብ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን እና ድርጅቱን ጠቅመዋል ተብለው ነው። ፖሊስ ተጠርጣሪው ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ወንጀል ጭምር ጠርጥሯቸዋል።

3፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ አወጣጥ ማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ ዛሬ የ14 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ መፍቀዱን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ችሎቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀድኩት ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ ነው ብሏል። ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተፈቀደባቸው የከተማዋ የቴክኒክ ሥልጠናና የቴክኖሎጂ ልማት እንዲሁም የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮዎች ሠራተኞች እና ሃላፊዎች ናቸው።

4፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን ማይክ ሐመርን ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን ሚንስቴሩ አስታውቋል። በውይይቱ ላይ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ ትሬሲ ጃኮብሰን ጭምር ተገኝተዋል። የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን፣ መንግሥት የምዕራባዊያን አምባሳደሮችና ልዩ መልዕክተኞች ወደ መቀሌ እንዲሄዱ መፍቀዱን ትናንት በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል።

5፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያውን ኤ350- 1000 ሞዴል ኤርባስ የመንገደኞችን አውሮፕላን ለመግዛት ማዘዙን አስታውቋል። አየር መንገዱ ግዙፉን የአውሮፓዊያኑን ኤ350- 1000 ኤርባስ የመንገደኞች አውሮፕላንን በመግዛት በአፍሪካ የመጀመሪያው ይሆናል። አየር መንገዱ አሁን ሊገዛቸው ያቀዳቸው አውሮፕላኖች፣ አራት ኤ350-1000 ሞዴል እና ሁለት ኤ350-900 ሞዴል ኤርባስ አውሮፕላኖች ናቸው።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ1427 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ1856 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 60 ብር ከ4377 ሳንቲም፣ መሸጫው 61 ብር ከ6465 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ52 ብር ከ9666 ሳንቲም ሲገዛ እና በ54 ብር ከ0259 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል። የቻይና ዩዋን ደሞ 6 ብር ከ9944 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ1343 ሳንቲም ተሽጧል።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)