Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ | ኢ.ዜ.አ

ሐሙስ ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እና በማናቸውም ጊዜ እና ቦታ ከሕወሃት ጋር ድርድር ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን አስታውቀዋል። መንግሥት ይህንኑ አቋሙን የገለጸው፣ ራሳቸው ሬድዋን እና ፍትህ ሚንስትር ጌዲዮን ዛሬ ከተመድ እና ከአውሮፓ ኅብረት ቋሚ መልዕክተኞች እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ብሪታኒያ አምባሳደሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።

2፤ የኢትዮጵያና ሩሲያ የጋራ ኮሚሽን በቀጣዩ ዓመት እንዲሰበሰብ እና አዳዲስ ስምምነቶች ላይ እንዲደርስ ከሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ስምምነት ላይ እንደተደረሰ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። ላቭሮቭ ሩሲያ ኢትዮጵያ ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ያለባትን እዳ ወደ ልማት መርሃ ግብር ለመለወጥ መወሰኗን ማስታወቃቸውንም መለስ ገልጸዋል። ላቭሮቭ ከፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ጋር ባደረጉት ውይይት ደሞ፣ አፍሪካ በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ሩሲያ ትደግፋለች ብለዋል። 

3፤ ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 61.3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል። የኩባንያው ገቢ የእቅዱ 87.6 በመቶ እንደሆነ የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። ኩባንያው በ2013 ዓ፣ም ያገኘው ገቢ 56.5 ቢሊዮን ብር ነበር። ኩባንያው ይህን ስኬት ያገኘው፣ በኃይል አቅርቦት እጥረት፣ በቴሌኮም አገልግሎት መቋረጥ፣ በነዳጅ እጥረት፣ በዋጋ ግሽበት፣ በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት እና በጸጥታ ችግሮች ውስጥ አልፎ መሆኑን ፍሬሕይወት ተናግረዋል።

4፤ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 27.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ዛሬ አስታውቋል። የባንኩ ጥቅል ትርፍ ከእቅዱ የ17.5 በመቶ ብልጫ አለው። የዘንድሮው የባንኩ ትርፍ ባለፈው ዓመት ካገኘው ጥቅል ትርፍ የ7.5 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማለትም የ43 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ባንኩ ገልጧል። ባንኩ ተቀማጭ ገንዘቡንም 890 ቢሊዮን ብር ማድረሱንና ጠቅላላ ሃብቱን ወደ 1.2 ትሪሊዮን ብር ከፍ አድርጌዋለሁ ብሏል።

5፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት ለቀጣዩ ዓመት 95 ቢሊዮን 320 ሚሊዮን ብር በጀት ማጽደቁን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ከዚሁ የክልሉ ዓመታዊ ጠቅላላ በጀት ውስጥ፣ 44 ቢሊዮኑ ከፌደራል መንግሥት ድጎማ እንደሚሸፈን ተገልጧል። ክልሉ ለቀጣዩ ዓመት ያጸደቀው በጀት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መድቦት ከነበረው በጀት የ15 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። ከበጀቱ ውስጥ ለድንገተኛ አደጋዎችና ክስተቶች 3 ቢሊዮን 499 ሚሊዮን ብሩ ለመጠባበቂያነት እንዲያዝ ምክር ቤቱ ወስኗል።

6፤ በአሜሪካ በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አስደናቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ እንድታገኝ ያስቻሉት ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ዛሬ በአዲስ አበባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በብሄራዊ ቤተ መንግሥት ፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተካሄደ ልዩ መንግሥታዊ ስነ ሥርዓት፣ መንግሥት ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ1338 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ1765 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 60 ብር ከ0540 ሳንቲም፣ መሸጫው 61 ብር ከ2551 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ52 ብር ከ8532 ሳንቲም ሲገዛ እና በ53 ብር ከ9103 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)