Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ግብርና ሚንስቴር ባለፈው ሰኔ 3 ምንነቱ ያ | ኢ.ዜ.አ

ማክሰኞ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ ግብርና ሚንስቴር ባለፈው ሰኔ 3 ምንነቱ ያልታወቀ የዶሮ በሽታ ገብቷል በማለት በዶሮና እንቁላል ላይ የጣለውን ክልከላ ሰኔ 27 ላይ ለክልሎች በከፊል ማንሳቱን ሰምተናል። በሽታው ባልታየባቸው አካባቢዎች ዶሮ አርቢዎች የዶሮ ስጋና እንቁላል እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው ሲሆን፣ በሽታው በታየባቸው አካባቢዎች ግን የዶሮ ስጋና እንቁላል ለገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች በቅድሚያ በሚንስቴሩ ላቦራቶሪ ማስመርመር አለባቸው። ሚንስቴሩ እስካሁን የበሽታውን ምንነት አላወቅንም በማለት ለዋዜማ ተናግሯል። አንድ የሚንስቴሩ ባለሙያ ግን በሽታው በጣም ተላላፊ መሆኑን አረጋግጠዋል።

2፤ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ባዋለው ችሎት በባሕርዳር ከተማ ቦምቦችን አፈንድተዋል ተብለው በእነ ቴዎድሮስ ጌታቸው መዝገብ በሽብር የተጠረጠሩ ተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ መዝጋቱ ተገለፀ። መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። ችሎቱ ግን የእስካሁኑ 24 ቀን በቂ መሆኑንና ማስረጃዎቹ ከመንግሥት ተቋማት የሚገኙ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሏል።

3፤ አምና በትግራዩ ጦርነት ሦስት ሠራተኞቹ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ መቀሌ አቅራቢያ የተገደሉበት የስፔኑ ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሃላፊ ፓውላ ጊል ወደ ትግራይ ክልል ለመጓዝ ከመንግሥት ፍቃድ እንዳላገኙ ድርጅቱ አስታውቋል። ሃላፊዋ ወደ መቀሌ ሂደው ድርጅታቸው በግድያው ላይ እስካሁን የደረሰበትን የውስጥ ግምገማ ለሁለቱ ሟቾች ቤተሰቦች ለማጋራት አቅደው ነበር። ሃላፊዋ በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ላቀረቡት ጥያቄም ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል። ለነፍስ አድን በድርጅቱ ተሽከርካሪ ሲጓዙ የተገደሉት፣ ዮሃንስ ሐለፎም፣ ቴዎድሮስ ገ/ማርያም እና ስፔናዊቷ ማሪያ ኸርናንዴዝ ነበሩ።

4፤ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የኡጋንዳ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል። ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ቆይታቸው፣ በሁለትዮሽና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ኮአፍሪካ ኅብረት ሃላፊዎች ጋር ይወያያሉ። ላቭሮቭ በአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት የበርካታ አፍሪካ አገራት ዲፕሎማቶችን በዝግ ለማነጋገር መጋበዛቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ላቭሮቭ ይህንኑ ውይይት የሚያደርጉት፣ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ በሚጓዙበት ዋዜማ ላይ ነው።

5፤ የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያ ማዕከል የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣን "አጣዳፊ ዓለማቀፍ የጤና ስጋት" በማለት መፈረጁን እንደሚያደንቅ አስታውቋል። በዓለም ዙሪያ እስካሁን የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከተገኘባቸው 75 አገራት መካከል፣ 11ዱ የአፍሪካ አገራት ናቸው። በዓለም ላይ ከ16 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም ባለፈው ሳምንት በሽታውን "የዓለም አጣዳፊ የጤና ስጋት" በማለት ያወጁት፣ የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች በጉዳዩ ሙሉ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ነበር።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ1213 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ1637 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 59 ብር ከ8853 ሳንቲም፣ መሸጫው 61 ብር ከ0830 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ53 ብር ከ2680 ሳንቲም ሲገዛ እና በ54 ብር ከ3334 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)