Get Mystery Box with random crypto!

እንላለን፡፡ በመሆኑም የመምህራኑ እና የደቀመዛሙርቱ ችግር ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ አንጻር ችግሩን በዘላ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

እንላለን፡፡ በመሆኑም የመምህራኑ እና የደቀመዛሙርቱ ችግር ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ አንጻር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአሁኑ የተሻለ ትኩረት እንዲደረግ ት/ትን፣ ስብከተ ወንጌልን ያካተተ የአብነት መምህራን ከበዙበት አካባቢ መምህራን ወደሌሉበት አካባቢ አህጉረ ስብከት ከእነበጀታቸው እየተዛወሩ እንዲያስተምሩ ተማሪዎቹም ባሉበት አካባቢ ቋንቋ እንዲማሩ በሚያስችል መልኩ የመማር ማስተማሩ ሥርአት እንዲቀጥል ጉባኤው አደራ ጭምር አሳስቧል፡፡
7. ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ ስኬታማነት ተናቦና ተግባብቶ መሥራት ሰባኪውና ተሰባኪው በቋንቋ በአመለካከት በአስተሳሰብ እንዲግባቡ ጥረት ማድረግ ብሔር ብሔረሰቦች በየልሳናቸው እንዲማሩ በዚህም ቃለ እግዚአብሔር ለሁሉም እንዲዳረስ የቤተ ክርስቲያናችን ዋነኛ ተልእኮ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአዳዲስ አማንያን ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት በተለይም አንድ የፕሮቴስታንት አማኝ ከእነ ተቋሙ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት በሌሎችም አህጉረ ስብከቶች ከሌሎች የእምነት ተቋማት እየተመለሱ የተፈጸመው ጥምቀተ ክርስትና ከቤተ ክርስቲያናችን የሚጠበቅ የአገልግሎት ውጤት በመሆኑ ጉባኤው በአክብሮት ተቀብሎታል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተደብቀው መዋቅሯን በመጠቀም የራሳቸውን የግል ፍላጎት ለማርካት የሚጥሩ ቢጽ ሃሳውያን አጥማቂ ነን፣ የዓለም ብርሃን ነን በሚሉ እና በልዩ ልዩ ስያሜ በየአህጉረ ስብከቱ ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን አዳራሾች ምእመኑን ግራ በሚያጋቡ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጥ እናሳስባለን፡፡

ስብከተ ወንጌል የመንግስተ እግዚአብሔር ቅዱስ አዋጅ እና ለሰው ልጅ የዘለዓለም ድህነት የተሰጠ ኪዳነ ሰላም ስለሆነ በመምሪያው በኩል ስምሪት በማዘጋጀት በተለያዩ አህጉረ ስብከት በሚከበሩ ክብረ በዓላትና አጿማት ሰባኪያነ ወንጌል እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል ለምእመናን እንዲያስተምሩ በትኩረት እንዲሠራ ጉባኤው አስገንዝቧል፡፡

በመንበረ ፓትርያርኩ የሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ውስን መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ ጋዜጦችና መጽሔቶች ስርጭታቸው ችግር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ጠቅላላ ተልእኮ ይሳካ ዘንድ ጋዜጦችና መጽሔቶች ያላቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያናችን ጋዜጦችና መጽሔቶች በሰው ኃይል በሊቃውንትም ተጠናክረው በብዛትና በጥራት እንዲታተሙ አቅም ያላቸው የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት እና የአብያተ ክርስቲያናት የሊቃውንት ተሳትፎ ያልተለያቸው ትምህርታዊ ጽሑፎችን እያሳተሙ እንዲያሰራጩ ጉባኤው አበክሮ ይጠይቃል፡፡
8. የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ በአሁኑ ወቅት የምታስተምራቸውን ት/ት ተምረው ቤተ ክርስቲያኒቱን ማገልገላቸው በታላላቆች አበይት የዓውደ ምህረት ክብረ በዓላት በየጊዜው የሚያሳዩት ሃይማኖታዊና አስተማሪ የሆነው የአሰላለፍ ስርዓት ከዓመት ዓመት እየደመቀ አስተማሪነቱ እየጨመረ መምጣቱ ዓለም በምልዓት እያደነቀው ያለ መንፈሳዊ ተግባር ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህ ውጤታማ እየሆነ የመጣውን ሂደት ለወደፊትም ለማስቀጠል እንዲቻል የሰ/ት/ቤት ማደራጃ መምሪያው በየደረጃው ዘርፉን በሰው ኃይል እና በማቴሪያል በማጠናከር ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው የቤተ ክርስቲያኒቱን ተረካቢና ተተኪ ትውልድ ማፍራት ወቅታዊ ጉዳይ ስለሆነ በሁሉም አቅጣጫ ትኩረት እንዲሰጠው ጉባኤው አጥብቆ ያሳስባል፡፡
በሰ/ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ ስር ያለው ማኅበረ ቅዱሳን በርካታ መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ልማታዊ ሥራዎችን እያበረከተ እንደሚገኝ በየአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶቹ ሪፖርት በስፋት ተገልጿል፡፡ ስለዚህም ማኅበሩ የዘረጋቸውን የአገልግሎትና የልማት አውታሮች ካለፈው የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው አሳስቧል፡፡
9. ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ጥንቃቄ በሊቃውንት ጉባኤ ሲዘጋጅ የቆየው የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ በበጀት ዓመቱ ለሕትመት በቅቶ በቅዱስነታቸው መመረቁ እና መጽሐፉ በሥራ ላይ እንዲውል መደረጉ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡ በቀጣይም የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ጉባኤ ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍቶች ጥንታዊነታቸውን ሳይለቁ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በስፋት ተዘጋጅተው እንዲደርሱ የማድረጉ ጥረቱን እንዲቀጥልበት በሚፈለገውም ሁሉ እገዛ እንዳይለየው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጉባኤው ይጠይቃል፡፡ በቀጣይም መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ እና በሌሎችም ቋንቋዎች መደበኛውንና ስርወ ቃል ትርጉም ባለቀቀ መልኩ እንዲታተም እና ለምእመናን እንዲሰራጭ ጉባኤው ይጠይቃል፡፡
10. ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ በዓለም የምትታወቅበት የነበረ ሃብቷ ሰላም አንድነት እና አብሮነት ሆኖ ሕዝቧን በፈርሃ እግዚአብሔር በበጎ ስነ ምግባር የሚታወቅ፤ የአየር ንብረቷ ለዜጎቿ ቀርቶ በውጭው ዓለም የሚገኙ የሚናፍቁት የሰው ልጆች መኖሪያና ምድረ ገነት መሆኗ ዓለም የተገነዘበው ሃቅ ነው፡፡ በእነዚህ በርካታ ዘመናትም በሀገሪቱ ውስጥ በመሪና በተመሪ በአጠቃላይ በዜጎች መካከል የነበረው የመከባበር እርስ በእርስ የመግባባትና የመፈቃቀር ሁኔታ አልፎ አልፎ እንቅፋት ቢያጋጥመውም የቀደሙ አባቶቻችን የነበራቸው የችግር አፈታትና ወደ አንድነት ለመመለስ ያደርጉት የነበረ ጥረትና ተቀባይነቱ በእጅጉ የሚያስመሰግን እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገራችን ዜጎች ሁሉ ለዚች እናት ሀገራችን ሲሉ ትላንት የነበረውን የመመካከርና የአንድነት ባህላቸውን አጥብቀው በመያዝ ለነገ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገራችን እንደምኞታችንና ሃሳባችን ካሰብነው ደርሳ ልማቷ አድጎ፣ አንድነቷ ተጠብቆ፣ ሕጻናት በሰላም የሚያድጉባት፣ ሽማግሌዎች የሚጦሩባት፣ የሁሉ ተስፋ የሆነች ሃገር እንድትኖረን ለማድረግ ጉባኤው ጥሪ እያቀረበ ሁላችንም ለሰላሙ መገኘት የዜግነት ድርሻችንን እንወጣለን፡፡ ከዚሁ ጋር በሀገራችን ያለው ጦርነት በሰላም እንዲፈታ ቤተ ክርስቲያን አዘውትራ የምትጸልይ ሲሆን መንግስት በየአቅጣጫው የጀመረውን የሰላም ሂደት ጉባኤው እያደነቀ በዚሁ እንዲቀጥልበትና እልባት ላይ እንዲደርስ ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ሰው ሁሉ በዚህ ዓለም ሲኖር ሠራተኛው ሠርቶ ለመበልጸግ፣ ነጋዴው ነግዶ ለማትረፍ፣ በሽተኛው ድኖ በጤና ለመኖር፣ ተማሪው ተምሮ ለማወቅ፣ በአጠቃላይ ዜጎች ማልደው ለመውጣትም ሆነ አምሽተው ለመግባት በምድራችን ሰላም ሲገኝ እርስ በእርስ መተማመን ሲኖር በመሆኑ ዜጎቻችን ለሰላምና ለአንድነት ተባብሮና ተከባብሮ ለመኖር እንዲችሉ የበኩላችንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
11. የሰላም እጦት በነበረባቸውና በጦርነቱ በተጎዱ የሀገራችን ክፍሎች ሕይወታቸውን ስላጡት ወገኖቻችን ጉባኤው ሐዘኑን እየገለጸ በመንግሥት በኩል የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለማከናወን በተያዘው እቅድ መሠረት የመከራውና የችግሩ ገፈት ቀማሽ ቤተ ክርስቲያናችን እንደመሆኗ መጠን በጦርነቱ የወደሙ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ፣ የተዘረፉ ንብረቶች እንዲተኩ፣ የፈረሱ መዋቅሮች መልሰው እንዲደራጁ፣ በሚመለከታቸው አካላትም እንዲታሰብበት ጉባኤው ያስገነዝባል፡፡