Get Mystery Box with random crypto!

ነሐሴ ፲፮ የብርሃን እናቱ የክብርት እመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋዋ በክብር ወደ ሰማይ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ነሐሴ ፲፮

የብርሃን እናቱ የክብርት እመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋዋ በክብር ወደ ሰማይ ያረገበት ዕለት ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት፡፡ ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ፡፡ እርሷም መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ለእነርሱ ነገረቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ጸለየች፡- ‹‹ልጄ ወዳጄ፣ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም ሕያዋን የሆኑትን ሐዋርያትን ሁሉንም ነፍሶቻቸውን የለየሃቸውንም ሁሉ ወደ እኔ አምጣቸው፤ አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን›› አለች፡፡

በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን አደረሰችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በፊቷ ሰገደላትና እንዲህ አላት፡- ‹‹ሰላምታ ይገባሻል፣ ጌታችንን ፈጣሪያችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሽው ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ከዚህ ዓለም ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና፡፡ ይህም ስሙ ክቡር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቅ ድንቅ ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ከገለጠ በኋላ ነው›› አላት፡፡ እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እግዚአብሔርንምእንዲህ ብላ አመሰገነችው፡- ‹‹ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን፣ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና፡፡ አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ ቅዱሳን መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ›› አለችው፡፡ በዚያም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ፡- ‹‹እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ፡፡ ሐዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ፡፡ ወዲያውም ሁሉም ሐዋርያት የሞቱት ከመቃብራቸው ተነሥተው በሕይወት ያሉትም ሁሉም ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት፡፡ ‹‹አምላካችን ከአንቺ የተወለደ ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ፣ እርሱ ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከእርሱ ጋር ያሳርግሻልና›› አሏት፡፡

በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠችና ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው፡- ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን ዐወቅሁ፡፡ ከዚህ ከሥጋዬ ወጥቼ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሄዳለሁ፡፡ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ፣ እኔ ከዚህ ዓለም እንደምለይ ከወዴት ዐወቃችሁ?›› ብላ የጠቀቻቸው፡፡ በመጀመሪያ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚያም ሁሉም ሐዋርያት ‹‹ወደ አንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን፣ በደመና ላይም በተጫን ጊዜ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን›› አሏት፡፡

እመቤታችንም ይህን ነገር ከሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፡- ‹‹ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈጽሜ አመሰግናለሁ፣ የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል›› አለች፡፡ ጸሎቷንም ስትጨርስ ሐዋርያትን ‹‹ዕጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት›› አለቻቸው፡፡ እነሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ፡፡ በዚያም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን እልፍ አእላፍ ቅዱሳን መላእክቱ አጅበው እያመሰገኑት መጣና እመቤታችንን አረጋጋት፡፡ ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት፡፡ በዚያም ጊዜ ድንቆቸ የሆኑ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ዓይነ ሥውራን ማየት ቻሉ፣ ደንቆሮች መስማት ቻሉ፣ ዲዳዎች ተናገሩ፣ ለምጻሞች ነጹ፣ ሐንካሶች መሄድ ቻሉ፣ ደዌ ያለበትም ሁሉ ዳነ፡፡ የብርሃን እናቱ ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ወደ አለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌአቸው ሁሉ ይፈወሳሉና፡፡

ከዚህም በኋላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጇን ‹‹በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሣ ከእሳት ባሕርም የተነሣ እፈራለሁ›› ባለችው ጊዜ እርሱም ‹‹እናቴ ሆይ ከእነርሱ ለማንም በአንቺ ላይ ሥልጣን የለውም›› አላት፡፡ ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትንና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት፡፡ እመቤታችንም እጇን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ጌታችን ቅድስት ንጽሕት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት። ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው፤ ወደ ጌቴ ሰማኒ ተሸክመው እንዲወስዷ ሐዋርያትን አዘዛቸው፡፡ ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃን እያየች ነበር፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችንም ‹‹እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ፡፡ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍሽ ጋር አዋሕጄ አስነሥቼ መላእክት በፊትሽ ሆነው በሚያመሰግኑበት አምሳያ በሌለው ተድላ ደስታ ባለበት መኖሪያ አኖርሻለሁ›› አላት፡፡

እመቤታችንም እንዲህ አለች፡- ‹‹አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሠራህ አመሰግንሃለሁ፤ ሁለተኛም ልመናየን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ፤ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወደ አንተ የሚለምነውን ከመከራም ሁሉ አድነው፤ በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሃሊ ነህና መታሰቢያየን በውስጧ የሚያደርጉባትን ቦታ ሁሉ ባርክ፣ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕታቸውን ተቀበል›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት፡- ‹‹የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ ደስ ይበልሽ፣ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህ ዓለምም በወዲያኛው ዓለምም ከቶ አይጠፋም›› አላት፡፡ እመቤታችንም በታላቅ ክብር ካረፈች

ኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሊወስዷት ሐዋርይት ገንዘው ተሸከሟት፡፡ አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊይቃጥሉ ወጡ፡፡ ከእርሳቸውም አንዱ ከምድር ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ፡፡ ያን ጊዜም ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋው ላይ ጠንጠለጠሉ፡፡ ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ፡- ‹‹የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ሆይ! አንቺ በእውነት ድንግል ይሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ አለምንሻለሁ፡፡›› በሐዋርይትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም እመቤታችንን በቀብሯት ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ፣ ዕረፍቷም የሆነው እሑድ ቀን ጥር ወር በ21 ቀን ነበረ፡፡ ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ላከ፣ እነርሱም ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሯት፡፡ በጌታችን ትእዛዝ መልአኩ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥጋ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር በክብር አኑሮታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ዮሐንስ ከተመለሰ በኋላ ‹‹እመቤታችን እንደምን አለች?›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም «ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ @Ethiopian_Orthodox