Get Mystery Box with random crypto!

' የመውጫ ፈተና የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ሆኖ ይቀጥላል ' - ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ሚኒስ | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

" የመውጫ ፈተና የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ሆኖ ይቀጥላል " - ትምህርት ሚኒስቴር

ትምህርት ሚኒስቴር ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ከዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና እና ከ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጋር ሳይጋጭ እንደሚከናወን አሳውቋል።

በ208 የትምህርት ፕሮግራሞች የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መዘጋጀቱንም ገልጿል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃል ፤ " የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ፣ ከመውጫና ከ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጋር በማይጋጭ መልኩ እንዲከናወን የሚረዳ ዕቅድ ተዘጋጅቷል " ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ፤ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ደግሞ ከሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ቀናት እንደሚሰጥ ዶ/ር ኤባ አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎቻቸውን የምረቃ መርሃግብር ከመውጫ ፈተና በኋላ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎቹ ምርጫ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሲጠናቀቅ ማካሄድ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ዶ/ር ኤባ ፤ በዘንድሮው ዓመት 180 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸው ለ208 የመመረቂያ ፕሮግራሞች የሚውሉ የፈተና ዓይነቶች መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል።

" የመውጫ ፈተና የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ሆኖ ይቀጥላል " ያሉት ዶክተር ኤባ፤ በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ተፈትነው 50 በመቶና በላይ ያመጡ ተማሪዎች እንደሚያልፉ አስረድተዋል፡፡

የመውጫ ፈተናው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑ የተማሪዎች ስም ዝርዝር ተልኮ ወደ ዳታ ማዕከል መግባቱን አመላክተዋል።

ለተማሪዎች ለፈተና የሚሆን ልዩ የመታወቂያ ቁጥር ይሰጣቸዋል ያሉት ዶክተር ኤባ፤ በተሰጣቸው ቁጥር መሠረት በኦንላይን መፈተን እንዲችሉ የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከል ደረጃ የተዘጋጀውን የፈተና ሥርዓት ለመሞከር እንደ አገር ሞዴል ፈተና እንደሚሰጥ አስታውቀው፤ በዚህም ጉድለቶች ካሉ ለማስተካከልና ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

ለፈተናው መሳካት ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተደራጀ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ለመውጫ ፈተናው የሚውሉ ኮምፒዩተሮች፣ የኢንተርኔት አገልግሎትና ጄኔሬተሮች ዝግጅት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።