Get Mystery Box with random crypto!

በአንዋር መስጊድ የነበረዉን 'ተቃውሞ አቀናጅታችኋል' የተባሉ ወጣቶች ከየቤቱ ታድነው እየታሰሩ ነዉ | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

በአንዋር መስጊድ የነበረዉን "ተቃውሞ አቀናጅታችኋል" የተባሉ ወጣቶች ከየቤቱ ታድነው እየታሰሩ ነዉ ተባለ

እስከአሁን የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነግሯል


ባሳለፍነው አርብ በአዲስ አበባ ከተማ፣ መርካቶ በሚገኘው አንዋር መስጊድ አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአማኙ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁት ደግሞ ከፍተኛ እና መካከለኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዘመድኩን ብሩ፤ "በዕለቱ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋግጧል" ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፤ ከሟቾች መካከልም አንድ ግለሠብ መታወቂያ ባለመያዙ ምክንያት እስከአሁን ማንነቱ ሊታወቅ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም፤ "ሰልፍ አቀናጅታችኋል" የተባሉ ወጣቶች ከየቤቱ ታድነው እየታሰሩ መሆኑን በመግለጽ፤ "ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል" ሲሉ ተናግረዋል።

ሟቾችን ለመቅበር የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ መዋቀሩን የተናገሩት ኃላፊው፣ ትናንት ቅዳሜ ግንቦት 26/2015 ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም መካነ መቃብር የአራት ምዕመናን ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ የቀሩትንም ወደ ትውልድ ሥፍራቸው በአስቸኳይ ለመሸኘትና ማንነቱ ያልታወቀውን ምዕመን ማንነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

"በተለያዩ ሚዲያዎች ሕዘበ ሙስሊሙ ምንም ዓይነት የተቃውሞ ድምጽ ሳያሰማ በሰላም ሰግዶ ሲወጣ ከጸጥታ ኃይሎች ተኩስ እንደተከፈተበት የሚወራው እውነት ነው ወይ?" የሚል ጥያቄ ከአዲስ ማለዳ ቀርቦላቸውም፤ "እሱን ገና በማጣራት ላይ ነን" ሲሉ መልሰዋል፡፡

በተያያዘ በዕለቱ፤ በጅማ ከተማ በተለያዩ መስጅዶች ተመሳሳይ ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር በሥፍራው የነበሩ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም መንቲና ወይም ሰቃ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ሙኒር መስጂድ፣ አጂፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ፈቲ መስጂድ እንዲሁም ሀሰን ጋራዥ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ራሕማ መስጂድ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ነግረውናል፡፡

በሥፍራው ከጠዋት ጀምሮ የጸጥታ ኃይሎች በብዛት ይታዩ እንደነበር የነገሩን የመረጃ ምንጫችን፣ የእምነቱ ተከታዮች ሰግደው ሲወጡ ከሰሞኑ እየፈረሱ ስላሉት መስጂዶች ድምጻቸው ማሰማታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ሰዓት በአካባቢው የነበሩት የጸጥታ አካላት የተኩስ ድምጽ ማሰማታቸውን የነገሩን ሲሆን፤ በዚህ የተደናገጡት የእምነቱ ተከታዮች ለመሸሽ በሚያደረጉት ጥረት በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

በሐረር፣ ሻሸመኔ እና ዶዶላ ከተሞችም መሰል ችግሮች ተከስተው እንደነበር በሥፍራው የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ቤተሰቦች ጠቁመዋል፡፡