Get Mystery Box with random crypto!

መንግሥት የሰዎች የመዘዋወር መብት ላይ የሚፈጸሙ ገደቦችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጠየቀ | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

መንግሥት የሰዎች የመዘዋወር መብት ላይ የሚፈጸሙ ገደቦችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጠየቀ

ሐሙስ የካቲት 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) መንግሥት ከሕግ አግባብ ውጪ በሰዎች የመዘዋወር መብት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ገደቦችን በአስቸኳይ እንዲያስቆም እና በዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና በአገር አቀፍ ሕጎች ላይ የተጣሉበትን ኃላፊነቶች እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጠየቀ።

ኢሰመጉ የሰዎችን የመዘዋወር፣ የአካል ነጻነትና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማግኘት መብት መንግሥት ያስከብር በሚል ርዕስ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የመዘዋወር ነጻነትን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጫዎችን በማውጣት በእዚህ መብት ላይ የሚጣሉ ተገቢ ያልሆኑ ገደቦች እንዲቆሙ ሲወተውት መቆየቱን አስታውሷል።

በመግለጫው በኢትዮጵያ ተገቢ ያልሆኑ ገደቦች ከሚጣልባቸው መብቶች አንዱ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት መሆኑን በማስታወስ፤ ምንም እንኳን ይህ መብት በዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ህጎች ላይ እውቅና ያለው ነገር ግን ፍጹም ያልሆነ የመብት አይነት ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢ ያልሆኑ ገደቦች እየተጣሉበት እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ኢሰመጉ የካቲት 3/2015 ባወጣው መግለጫ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ሰዎች ከመንገድ እየተመለሱ መሆኑን እና በእዚህም ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው መንገደኞች እየተንገላቱ መሆኑን በመግለጽ ይህ ድርጊት እንዲታረም ጥሪዎችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ምንም አይነት የእርምት እርምጃዎች ሳይወሰዱ ይልቁንም ጉዳዩ ዳራውን በማስፋት ከደብረብርሀን፣ ከባህርዳር፣ ከደብረዘይትና ሌሎችም አካባቢዎች ጭምር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ መንገደኞች ያለምንም በቂ ምክንያት እየተመለሱ መሆኑን እና በእዚህም ምክንያት ለተለያዩ ጉዳዮች ሕክምናንም ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎሉ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን ገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት፤ በሰዎች የመዘዋወር መብት ላይ የሚደረገው ገደብ ምንም አይነት ሕጋዊ መሰረት የሌለው፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ እንዲሁም አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ በመሆኑ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ በተለየዩ ኬላዎች ላይ የሚገኙ የመንግስት የጸጥታ አካላት ከእዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊት እንዲቆጠቡ፣ ይህንንም ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን መንግስት በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስቧል።

በተጨማሪ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በሚገኙ አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እየታሰሩ ይገኛሉ፡፡“ ያለው ኢሰመጉ፤ በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በብዛት የሚፈጸሙ ተገቢውን የሕግ ሥነ ስርዓት ያልተከተሉ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ ይህ ድርጊት አሁንም ምንም አይነት ዘላቂ መፍትሄ ባለማግኘቱ ድርጊቱ እየተበራከተ እንደሚገኝ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡

የፌደራል እንዲሁም የሚመለከታቸው የክልል መንግስታት ከሕግ አግባብ ውጪ በብዛት የሚፈጸሙ ሕገወጥ እስሮችን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙም ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል፤ ትናንት የካቲት 8/2015 በወልቂጤ ከተማ ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ የከተማው ነዋሪዎች “ችግሩ እንዲፈታልን” በማለት ቅሬታቸውን ለመግለጽ ጀሪካን ይዘው አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች ላይ፤ የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል በወሰደው እርምጃ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ኢሰመጉ ገልጿል፡፡

የደቡብ ክልል መንግስት በወልቂጤ ከተማ የተከሰተውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በአስቸኳይ በመፍታት ማሕበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማግኘት መብቱን እንዲያከብር፤ እንዲሁም ይህ እንዲሟላላቸው በጠየቁ ዜጎች ላይ የሞት እና ሌሎች አደጋዎችን ያደረሱ የፀጥታ አካላት በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲደረጉ ኢሰመጉ በመግለጫው አሳስቧል፡፡