Get Mystery Box with random crypto!

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አፈጻጸም አዝጋሚ መሆኑ ተገለጸ ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 (አዲስ | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አፈጻጸም አዝጋሚ መሆኑ ተገለጸ

ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአፍሪካ አገራት መካከል ነጻ የንግድ ቀጠና ለመመስረት ከኹለት ዓመት በፊት ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ እጅግ አዝጋሚ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ በቅርቡ የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ በዓለም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ ካሉ 55 አገራት በአምስት አገራት ብቻ ስምምነቱ በከፊል እየተተገበረ እንደሚገኝ ነው የተመላከተው፡፡

የአፍሪካ መንግስታት ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት አናሳ በመሆኑም፣ በቂ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት አለመኖር፣ ግልጸኝነትና ቅልጥፍና የጎደላቸው አሰራሮች እንዲሁም የኮሮና ወረርሽኝ እና የፀጥታ ችግሮች ስምምነቱ እንዳይተገበር ትልቅ እንቅፋት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

በአውሮፓ አገራት መካከል ያለው ነጻ የንግድ ልውውጥ ከ66 በመቶ በላይ፣ በእስያ ከ63 በመቶ በላይ እንዲሁም በአሜሪካ ከ44 በመቶ በላይ ሲሆን፣ በዓለም ዝቅተኛ የሆነውና በአፍሪካ አገራት መካከል ያለው ነጻ የንግድ ልውውጥ ግን ከ13 በመቶ በታች መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአህጉሪቱ ያለው ስር የሰደደ የፀጥታ ችግር እና ብልሹ የአስተዳደር ሁኔታ የነጻ ንግድ ልውውጡን የወደፊት ተስፋ የሚያጨልም ነው ተብሏል፡፡

የአፍሪካ መንግስታት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ልውውጥ እንዲያድግ በሰዎች ነጻ ዝውውርና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የመስራት አቅም በየዓመቱ እያሽቆለቆለ መምጣቱም ነው የተነገረው፡፡

በዚህም አህጉሪቱ የውስጥ አቅምን ከማሳደግ ይልቅ በውጭ ገበያ ላይ ጥገኛ በመሆኗ ውስጣዊ የኢኮኖሚ ቀውሱ ተባብሶ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡ በፈረንጆች 2021 ከኤርትራ በስተቀር ኹሉም አገራት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ቢደረግ አህጉራዊ የንግድ ልውውጡን በ40 በመቶ እንደሚያሳድገው ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ልውውጥ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 42ኛው የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች ጉባኤ፣ እዲሁም 36ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡