Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ ማከናወን የተራዘመባቸው ክልሎችን አስመልክቶ የተሰ | ESAT International

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ ማከናወን የተራዘመባቸው ክልሎችን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ለ6ተኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ የተለያዩ ተግባራትን እየፈጸመ እንደሆነ ይታወቃል።

ቦርዱ በማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ (1) እና የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ (7) እና አንቀፅ 163 ንዑስ አንቀፅ (2) ላይ በተሰጠው ሥልጣን ባወጣው የዕጩዎች ምዝገባ መመሪያ መሠረት፤ የዕጩዎችን ምዝገባ ለማከናወን የሚያስችሉትን ከክልል መስተዳድሮች እና ከከተማ መስተዳድሮች የሚጠበቁ የትብብር ግዴታዎችን ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ገልፆ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደነበር ይታወቃል።

በዚህም መሰረት የክልሎች ዝግጁነት ምን እንደሚመስል ሰኞ የካቲት 01 ቀን 2013 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

በመግለጫውም
• አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
• ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
• ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
• ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
• ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና
• ሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስፈላጊ የሆኑትን ለምርጫ ክልል እና ለዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቢሮዎችን አዘጋጅተው ለቦርዱ እንዳስታወቁ በመግለጽ፤ በጊዜ ሠሌዳው በተቀመጠው ቀን መሠረት ከየካቲት 08 እስከ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የዕጩ ምዝገባ የሚከናወነው ከላይ በተጠቀሱት ክልልሎች በሚገኙ የምርጫ ክልል ቢሮዎች መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን በቀሪዎቹ ክልሎች የክልል መስተዳድሮቹ ደግሞ አስፈላጊውን ትብብር ሲያደርጉ ምዝገባው የሚጀመርበትን ቀን ቦርዱ የሚያሳውቅ ገልፆ ነበር።

መሆኑን በዚሁ መሠረት እጩ ምዝገባ በማይጀመርባቸው ቀሪ ክልሎቹ የሚካሄዱት የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት እንደሚከተለው ይሆናል፤
• አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
• አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
• ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
• ደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት እና
• ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከየካቲት 05 እስከ የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ለዕጩዎች ምዝገባ የሚውሉ ቁሳቁሶች የሚጓጓዙበትና የዕጩዎች ምዝገባ አስፈጻሚዎች ሥልጠና የሚሰጥበት ጊዜ ሲሆን፤ ከየካቲት 15 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ የዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወንበት ጊዜ እንዲሆን ቦርዱ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የካቲት 06 ቀን 2013 ዓ.ም

@ethiomereja1 ሼር