Get Mystery Box with random crypto!

በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል የመሳሪያ ብልሽት አጋጥሟል በሚል የኩላሊት ህመምተኞች የዕጥበት አገልግሎት | Ethio Fm 107.8

በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል የመሳሪያ ብልሽት አጋጥሟል በሚል የኩላሊት ህመምተኞች የዕጥበት አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸዉን ተናገሩ፡፡

ስምንት እና ከዚያ ዓመት በላይ በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ዕጥበት ሲያደርጉ ነበሩ ፣ ወደ 43 የሚጠጉ የኩላሊት ህመምተኞች ቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ማጠብ ስላልቻለ ከአለፉት 15 ቀናት ጀምሮ በሚኒሊክ ሆስፒታል ተባባሪነት የዕጥበት አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበር ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሚኒሊክ ሆስፒታል ለ 15 ቀናት ያህል የዕጥበት አገልግሎት ስናገኝ ብንቆይም ባሳለፍነው ቅዳሜ ለመታጠብ ስንሄድ ማክሰኞ እንዳትመጡ በሚል ከሚኒሊክ ሆስፒታል ወጥተናል ፣ ወደ ጳዉሎስ ሆስፒታል ብንሄድም፤ ሆስፒታሉ ምንም ማድረግ ስለማልችል በግላችሁ ታጠቡ የሚል ምላሽ ሰጥቶናል” ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ቅሬታቸዉን አቅርበዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ ለማጣራት ወደ የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ጋር ደዉለን ያለዉን ነገር ስንጠይቅ ከዘዉዲቱ ሆስፒታል ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል አስፈላጊዉ የማጠቢያ አሲድ እንዲላክ መነጋገራቸዉን እና አሲዱ ለሚኒሊክ ሆስፒታል መድረሱን ማረጋገጣቸዉን ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በድጋሚ ቅሬታ አቅራቢዎቸን ስናነጋግር ምንም ዓይነት የተሰጣቸዉ መፍትሄ እንደሌለ እና አሁን ባለው ሁኔታ ዛሬም ፣ነገም ሆነ ከነገ በስትያ የኩላሊት ዕጥበት ማግኘት የሚችል ታካሚ አለመኖሩን ነግረዉናል፡፡

ከኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበርም የተሰጣቸዉ ምላሽ ተገቢ ያልሆነ መሆኑንም ነዉ ጨምረዉ የነገሩን፡፡

የሚኒሊክ ሆስፒታል የማጠቢያ ማሽን የአገር ዉስጥ አሲድን ስለማይቀበል የቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ማሽን ቢሆንም አገልግሎት ሊሰጠን የሚችለዉ ፣ የሆስፒታሉ ማሽን በመበላሸቱ ምንም ለማድረግ አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በትናንትናው እለት ጤና ሚኒስቴር ሄደዉ እንደነበር የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሁሉም ስብሰባ ላይ በመሆናቸዉ ተመልሰዉ መምጣታቸዉን ገልጸዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር አሲዱ ተገዝቶ ጉምሩክ ላይ መሆኑን ነግሮናል ያሉን ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታልም ችግሩን ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን እንዳሳወቃቸዉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር በበኩሉ በትናንትናው ዕለት አገልግሎቱ በሚኒሊክ ሆስፒታል መጀመሩንና ለታካሚዎች እየተደወለ የዕጥበት አገልግሎት ሲሰጣቸዉ እንደነበር ማረጋገጡን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አሰፋ ነግረዉናል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሐምሌ 13ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

YouTube

https://www.youtube.com/.../UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos