Get Mystery Box with random crypto!

ሬናሰንት የተሰኘ የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ተሃድሶ ማዕከል ተመርቋል። በሱስ እና የአዕምሮ ጤና ች | Ethio Fm 107.8

ሬናሰንት የተሰኘ የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ተሃድሶ ማዕከል ተመርቋል።

በሱስ እና የአዕምሮ ጤና ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ለመሆን በሱስ የስነልቦና ባለሙያዎች ፣ በኤክስፐርት የስነልቦና ባለሙያዎች እና በስነልቦና ነርስ ባለሙያዎች አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ማዕከል ነው በትናንትናው እለት በይፋ የተመረቀው።

ማዕከሉ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረ ጥቂት ወራትን ያስቆጠረ ነው ያሉት የማዕከሉ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ናቸው።

ፕሮፌሰሩ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት አጭር ጊዜ ውስጥ ከመቶ በላይ ተገልጋዮች ተኝተው ህክምና ያገኙ መሆናቸውን ገልፀው ፣ አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ30 አመት በታች የሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የሴቶች ፣ ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የእንደዚህ አይነት ማዕከላት መገንባት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ሙሉ ድጋፍ የሚያገኝ እና ሌሎች ተመሳሳይ ማዕከላት እንዲገነቡም መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል።

ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደ አገር ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ የወጣት ማዕከላት መኖራቸውን አንስተው ትናንት ከተመረቀው ማዕከል ጋር በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በ2007 ዓ.ም በተደረገው እና በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10ሺህ ሰዎች በላይ የተሳተፉበት ጥናት፣ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15-65 የሆኑ ወንዶች የአልኮል ሱሰኞች ነበሩ ተብሏል፡፡
16 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የጫት ሱስ እና 5 በመቶ የሚሆኑት የትምባሆ ሱሰኞች እንደነበሩ ጥናቱ ያሳያል።

በእስከዳር ግርማ
ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም