Get Mystery Box with random crypto!

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል የሰጡት ሙሉ መግለጫ! በትግራይ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል የሰጡት ሙሉ መግለጫ!

በትግራይ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት አስመልክቶ “ህዝቡ ራሱን በራሱን የማስተዳደር መብቱን በተግባር ለማረጋገጥ በፅናት ስለታገለ የተቃጣበት ጦርነት” ያሉት ሲሆን አራት መንግሥታትና የክልሎች ልዩ ኃይሎች ተሳትፈውበታል ብለዋል።

አራቱ ብለው የጠሯቸው መንግሥታት እነማን እንደሆነ ባይዘረዝሩም “በዚህም ምክንያት የኃይል አለመመጣጠን አጋጥሟል” በማለት አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያለው ትግል እንደቀጠለና በክልሉ ከነበረው ሰሜን እዝ የተገኘውን ኃይል በመጠቀም እየታገሉ መሆናቸውን አስታውሰው ” በኃይል አለመመጣጠን ምክንያት ጊዜያዊ ወታደራዊ ብልጫ ስላገኙ ይህንን ሚዛን ለመለወጥ የመመከት ትግላችንን አጠናክረን እያስቀጠልን እንገኛለን።” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት እንደሌለና እየተደረገ ያለው የህወሓት አመራሮችን በማደን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።

የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሰራዊት ቁጥጥር መግባቱን ተከትሎ ከሰዓታት በኋላ የህወሃት ሊቀ መንበር ከሮይተርስ ጋር በመልዕክት ባደረጉት ንግግር ትግሉ እንደሚቀጥልና “ትግሉ የራስን መብት በራስ የመወሰን እንደሆነ” ተናግረው ነበር።

በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ከነዚህም አመራሮች አንዱ የህወሃት ሊቀ መንበር ደብረ ፅዮን ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ያሉበት አይታወቅም።

ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል በጠቀሱት ትግል “ከፍተኛ ዋጋ ጠይቋል” ያሉ ሲሆን። “የህወሃት መስራች አባላት ከሚባሉት ላለፉት 45 ዓመታት ከያዙት ህዝባዊ መስመር ፈቀቅ ሳይሉ የታገሉና የመሩ፣ ያታገሉና ብዙ ድል ያስመዘገቡ አዛውንት ነባር ታጋዮች በዚህ የወረራ ጦርነት፣ በጠላት እጅ ተጎድተውብናል። ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ። የነዚህ ጀግኖቻችን መስዋዕትነት የበለጠ ቁጭትና እልህ ያስንቀናል እንጂ ፈፅሞ ከትግላችን የሚያቆመን አይሆንም።” ብለዋል

ዶ/ር ደብረፅዮን መስዋዕት ሆነዋል ያሏቸውን ግለሰቦች በስም ባይጠቅሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ በተለያዩ የሥልጣን ቦታ ላይ የነበሩት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊቱ ከድተዋል የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስ በግጭቱ ወቅት እጅ አልሰጥም በማለታቸው መገደላቸው ተነግሯል።

ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በክልሉ ላይ ደረሱ ስላሏቸው ጥቃቶችና ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመዘርዘር ተናግረዋል።

“የትግራይ ሴቶች በተናጠልና በደቦ ይደፈራሉ። የትግራይ ሰዎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች በከፋ መገለጫና አኳሃን ይጣሳሉ፣ ይገፈፋሉ። የትግራይ መንደሮችና ዓብያተ እምነቶች፣ የትግራይ ሰራዊት ይኑርበት አይኑርበት ሳይገዳቸው የቦምቦችና የመድፎ ዒላማ ይደረጋሉ። ውድና መተኪያ የሌላቸው ቅርሶችም ይወድማሉ፣ ይዘረፋሉ። በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዳለ ከቀየው ወጥቶና ተፈናቅሎ የመከራ ኑሮ ይኖራል።” ብለዋል።

ደብረ ፅዮን ህዝቡ ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉትን ወንጀል በግልፅ እንዲቃወምና እንዲያወግዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ተፈፀመ ያሉት ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው ለዚህ ተጠያቂ ናቸው ብለው የጠሯቸውን የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።

ደብረ ፅዮን በትናንትናው መልእክታቸው በአሁኑ ወቅት በርካቶች ወደ ትግሉ ሜዳ እየጎረፉ እንደሆነ ገልፀው ህዝቡ ያለ አንዳች ልዩነት “ጠላት” ብለው የጠሩትን ኃይል እንዲታገሉ ጠይቀዋል።

ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባስተላለፈት መልእክት፣ በጦር ሜዳው፣ መድረኩም ሆነ፣ ድምፅ በማሰማትና በሌሎች መድረኮች ላይ ትግሉ እንደቀጠለ አስታውሰው “ሌሎቻችሁም በፍጥነት የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ።” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ትግሉ እስከመጨረሻ እንደሚቀጥል ባስተላለፉበት በዚህ መልዕክት “እኛ ከመሬታችን እና ከቀያችን ለቀን የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለንምና የተሟላ ድል እስክንቀዳጅ ህዝባዊ ጦርነት ከማፋፋም ወደ ኋላ እንደማንል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል።” በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

የደብረ ፅዮንን ንግግር በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

ምንጭ : ቢቢሲ አማርኛ

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news