Get Mystery Box with random crypto!

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲዳራጅ ተወሰነ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር | ኢትዮ መረጃ - NEWS

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲዳራጅ ተወሰነ

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት በዛሬው ቀጣይ ዉሎው የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተካተቱበት «የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል» በሚል ስያሜ አዲስ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፏልመደበኛ ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባካሄዱት ሕዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአንድ ክልል እንዲደራጁ በዛሬው እለት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ መወሰኑን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል፡፡

«የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል» በሚል በአዲስ የተደራጁት በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጌዲዮ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ ዞኖችና በደራሼ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በኧሌና በባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡    

ቀድሞ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ውስጥ የነበሩ የሀድያ፣ የሀላባ፣ የከምባታ ጠምበሮ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ  ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ ክልል የሚቀጥሉ ይሆናል።

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛው የፓርላማ ዘመን፣ በ1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜው ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ በስድስት ዘኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ የጌዴኦ ፣ የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዘኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የኧሌ ልዩ ወረዳዎች  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ክልል ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47/3/(ለ)መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጂ እና በጋራ ክልል የመመሥረት ጥያቄው የሕዝቡን ይሁንታ ስለማግኘቱ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መምራቱ ይታወሳል::

በመጨረሻም የተከበሩ አፈ ጉባኤ  አቶ አገኘሁ ተሻገር የውሳኔ ሀሳቡ እንዲጸድቅ ለድምጽ አቅርበው ቤቱ በሙሉ ድምጽ ደግፎ አጽድቆታል።

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news