Get Mystery Box with random crypto!

እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል ተባለ!! በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከተደ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል ተባለ!!

በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገበት 2010 ወዲህ ባሉት ዓመታት ከ25 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ የሚገመቱ የአማራ ተወላጆች በአክራሪ ብሔርተኞች መገደላቸውን ካውንተር ፓንች በድህረ ገጹ አስነብቧል።

ዘገባው አብዛኞቹ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚል በሚጠራው እና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በተፈረጀው ኃይል የተገደሉ መሆናቸውን መገለጹን አዲስ ማለዳ ከድህረ ገጹ ዘገባ ተመልክታለች፡፡

ከዚህ ባለፈም፤ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው ነው የተገለጸው። እንዲሁም በአገሪቱ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው የተባለ ሲሆን፤ የመሰበሰብ፣የሚዲያ ነጻነት እና ሌሎች ተያያዥ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አደጋ ውስጥ መግባታቸው ተጠቅሷል።

በዚህም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የአገር ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣በግልጽ የሚናገሩ ጋዜጠኞች እና የግል የሚዲያ ተቋማት በነጻነት የመናገርና የመስራት መብታቸውን አጥተዋል ሲል የካውንተር ፓንች ዘገባ አመላክቷል።

ዘገባው መሰረቱን በአሜሪካ ያደረገ“ፍሪደም ሃውስ”የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትን መረጃ ጠቅሶ፤በኢትዮጵያ በስፋት መንግሥትን የሚተቹ አካላት ከእውቅናቸው ውጭ በሆነ መንገድ በመንግሥት የደህንነት አካላት በእጅ ስልካቸው ላይ ሳይቀር ሚስጥራዊ ክትትል እንደሚደረግባቸው ጠቁሟል።

በአገሪቱ የዘፈቀደ እስራት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም በመጥቀስም፤ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታቸው ወይም ከመንገድ ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በደህንነቶች ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ እንደሚወሰዱም ተገልጿል።
 
@ethio_mereja_news