Get Mystery Box with random crypto!

በአዲስአበባ ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ሰዎችን በሀይል የመሰወር ድርጊት ተባብሷል ሲል ኢሰመኮ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

በአዲስአበባ ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ሰዎችን በሀይል የመሰወር ድርጊት ተባብሷል ሲል ኢሰመኮ አስታወቀ

ድርጊቱ በአፋጣኝ ሊቆም እንደሚገባም አሳስቧል!!

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከደረሱት አቤቱታዎችና ጥቆማዎች በመነሳት ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሠረት በርካታ  የአስገድዶ መሰወርን ድርጊት የሚያቋቁሙ ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

በተለይም ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በተከሰተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎች በማነጋገር፣ በልዩ ልዩ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች በመዘዋወር እና ከቤተሰቦችና ከሌሎች የመረጃ ምንጮች መረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ብስራት ራዲዮ ከኮሚሽኑ ካገኘዉ መረጃ ተመልክቷል።

አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ  እንዲሰወሩ የተደረጉ ሲሆን ፤ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸው ገለጿል። ሆኖም አሁንም ግን ሌሎች  ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ ናቸው ብሏል ኮሚሽኑ።

ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው ሲል በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በማስገደድ ተሰውረው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከተለያየ የጊዜ መጠን መሰወር በኃላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የተገኙ ሲኖሩ፣ አስገድደው በተሰወሩበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የቀድሞው ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደቆዩ ለመረዳት ተችሏል። በአስገድዶ መሰወሩ ወቅት ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ወይም የማሰቃየት ተግባር ኮሚሽኑ ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀ ትክክለኛውን መረጃ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ፤ “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች ሁሉ እንዲወስድ፣ የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል። 

የአስገድዶ መሰወር ወንጀልን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ ልታጸድቅ እንደሚገባም አሳስቧል።

በሌላ በኩል አንድን ሰው የሚገኝበትን ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር መያዝ ማለት በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሯል የተባለን ሰው ለወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት ከቤተሰብ እና ከጠበቃ እንዳይገናኝ አድርጎ በእስር የማቆየትን ተግባር ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው ብሏል።

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news