Get Mystery Box with random crypto!

በመስኪዶች አካባቢ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ተቀራርቦ መነጋገር አማራጭ የሌለው | ኢትዮ መረጃ - NEWS

በመስኪዶች አካባቢ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ተቀራርቦ መነጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ ተገለፀ።

በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች መሰኪድ ፈርሷል በሚልየተፈጠረዉንችግር ከሚመለከተው አካል ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገርና የጋራ መፍትሄ ለማበጀት በፌዴራል እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት አማካኝነት የተቋቋመ ኮሚቴ ከኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ብናልፍ አንዷለም ጋር ተወያይቷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከፌዴራል መጅሊስ ፣ ከአዲስ አበባ መጅሊስ እና ከኦሮሚያ መጅሊስ የተወከሉ የሐይማኖት አባቶች በሰላም ሚኒስቴር ፅ/ቤት የተገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተገኝተዋል።

በተለይ በመስኪዶች አካባቢ ላጋጠመው ችግሮች ከሚመለከተው የትኛውም የመንግስት አካል ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማመንጨትና ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ የተቋቋመ ኮሚቴ መሆኑን ከመጅሊስ ተወክለው የመጡት አመራሮች ገልፀዋል።

መስኪዶች በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ፈርሰዋል በሚል ምክኒያት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁለት መስኪዶች ላይ በሁለት የጁምዓ ሶላት ቀናት አመፅ ለመቀስቀስ ሞክረዋል። እነዚህ አካላት በቀሰቀሱት ግጭት ምክኒያት የንብረትና የአካል ጉዳት እንዲሁም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። ይህ አላስፈላጊ ጉዳት መድረሱ በፍፁም አግባብ እንዳልነበረና ከመፈጠሩ በፊት ሊወገድ የሚችል ችግር እንደነበር በዚህ ውይይት ላይ ለመግባባት ተችሏል።

የመጅሊስ ተወካይ የኮሚቴው አባላት በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት ለሚፈጠሩ ማንኛውም ችግሮች ተቀራርቦ መነጋገርና መወያየት መፍትሄ ያመጣል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ዘብ እንዲሁም ግንባር ቀደም የሰላም ጠበቃዎችም ናቸው ያሉ ሲሆን፣ የትኛውንም ችግር መፍታት የሚቻለው በንግግርና በውይይት ብቻ መሆን አለበት ብለዋል።

የተፈጠሩት ችግሮች ከሀይማኖቱ አባቶች እና ከመንስት አቅም በታች በመሆናቸው ይህ ኮሚቴ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በቅርበት መነጋገር መጀመሩ የሚበረታታ ነው ያሉት አቶ ብናልፍ አፋጣኝ መፍትሄም እንደሚያስገኝ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል

ይህ ኮሚቴ ለዚህ ወቅታዊ ችግር መፍትሄ በጋራ ማፈላለግ ዋነኛ ተልዕኮው ነው ያሉት አቶ ብናልፍ በዚህ አላስፈላጊ ግጭት ምክኒያት ያጋጠሙ ጉዳቶችና ጥፋቶች ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።