Get Mystery Box with random crypto!

#የቀጠለ በእዛ ቀን የለበስኩት ጥቁር ነበር፡፡ ሸበላዉ ምናልባት ዛሬ ይመጣ ይሆናል፡፡ ጥቂት ተስተ | ልብወለድ Ethio_Fiction

#የቀጠለ
በእዛ ቀን የለበስኩት ጥቁር ነበር፡፡ ሸበላዉ ምናልባት ዛሬ ይመጣ ይሆናል፡፡
ጥቂት ተስተናጋጆች ናቸዉ ቡና ቤቱ ውስጥ ያሉት፡፡ አዜብ (ቅፅል ስሟ ሩት፡፡ ሁላችንም የሥራ ቦታ ቅፅል ስም አለን) ከእኔ ተቃራኒ ካለዉ ወንበር ላይ ተቀምጣ ቦርሳ ዉስጥ በምትያዝ ትንሽዬ የፊት መስታወት ላይ አተኩራ ፊቷን በማስዋብ ተግባር ላይ ተጠምዳለች፡፡ የምሸሸዉን ትዝታ የሚጎትት የኩኩ ሰብስቤ ዘፈን ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ስፒከሮች በኩል ጐላ ብሎ ይንቆረቆራል፡
 የሰማዩ ዝናብ ከዳመናዉ መጣ
 ከዐይኔ የሚመነጨዉ ኧረ ከየት መጣ?
ተመራምሬያለሁ እኔ ግን በሐሳቤ
ዕንባዬ የመጣዉ ነዉ እኮ ከልቤ
ክረምት አልፎ በጋ ሁሌ አይቀርም ሲባል
የእኔ ዕንባ አላባራም ገና ነዉ ይዘንባል
ከአንጀቴ ከሆነ ዕንባዬ የሚፈሰዉ
ምክንያቱ አንተ ነህ አላዉቅም ሌላ ሰዉ
እኔ እወድሃለሁ ፍቅሬ አስብሃለሁ
ይወቴ በሙሉ ያንተ ነዉ ብያለሁ።

ሲጋራዬን እያቦነንኩ ዘፈኑን ተከትዬ በትዝታ እየተብሰከሰኩ ሳለ ከእኔ እኩል እዚህ ቡና ቤት ግልሙትና የጀመረችዉ መክሊት (ቅፅል ስሟ ሮዛ) በቡና ቤቱ የጀርባ በር በኩል ዘልቃ እየተጣደፈች መጥታ ጉንጬን ሳመችና ባልኮኒዉ አጠገብ ተሰብስበዉ ለሚያወጉት ሴቶች ለስንብት እጇን አዉለብልባ ቤቱን ለቃ ተሰወረች፡፡ አጠገቤ መጥታ ሳለ ነስንሳዉ የሄደችዉ ስርንን የሚበጥሰዉ ርካሽ ሽቶዋ ጠረን ገና በአየር ተጠርጎ ስላልተወሰደ ምቾቴን አጓድሎታል፡፡ መክሊት እዚህ ቡና ቤት ሥራ የጀመረችዉ ከእኔ ቀድማ ነዉ፡፡ በቀለም ትምህርት እስከ ኮሌጅ ገፍታለች እየተባለ ስለሚወራ ‘ምሁሯ’ የሚል የአግቦ ስም ሰጥተናታል፡፡ ከእሷ በቀር እዚህ ቡና ቤት የምንሠራ ብዙዎቻችን ከሃይስኩል አልዘለቅንም፡፡

ደግሞስ ቀለም ለሴት ልጅ ምን ይፈይዳል? ሴት ልጅ ቁንጅና ይኑራት ብቻ፡፡ መልክ ካለ ሁሉ አለ፡፡
ይህን ብሽቅ ሥራ እየሠራሁ ረብጣ ገንዘብ አፍሳለሁ፤ ግን ይህ ነዉ የሚባል የአፈራሁት ጥሪት የለም፡፡ የዘወትር ጥረቴ የዕለት ቀዳዳዬን ከመሙላት ዘሎ አያዉቅም፡፡ ማለቴ የወደፊት ዕጣዬን በቀቢፀ ተስፋ የምጠብቅ ሰዉ ነኝ፡፡ ደግሞስ የወደፊቱን ጊዜ አስረግጦ መተንበይ የሚችል ማን ነዉ? ሰዉ በዕጣ ፈንታዉ እግረ ሙቅ የተጠፈረ ፍጡር ነዉ፡፡ ማለቴ ሕይወት ከሰዉ ልጅ ትልም አፈንግጦ በዘፈቀደ በራሱ ቅያስ የሚነጉድ ነዉ፡፡ እናም የሰዉ ድካም ከንቱ ነዉ፡፡ እነሆ ለምሳሌ፣ ከቀናት በፊት የምሠራበት ቡና ቤት ባለቤት ወይዘሮ ሮማን ብቸኛ ልጅ በሠርጓ ዋዜማ እንደ ሸክላ ተሰበረች፣ ገና በለጋ ዕድሜዋ፡፡ ያ ሁሉ ልፋቷ  በሞት ተደመደመ፡፡

አሁን እንደዉ ያን ዉብ ገላ ምስጥ ይበላዋል? የሰዉነት ፋይዳ ምንድን ነዉ? ሰዉ ከትቢያ የሚልቅ ዋጋ አለዉን? ሰዉ ከጉንዳን፣ ከድንጋይ፣ ከአሸዋ፣ ከአፈር በምን ሚዛን ይልቃል? ሕይወት ፋይዳ ቢስ አይደለምን? በየትኛዉም ቅፅበት እንዳልነበር የሚሆን ወረት፡፡   
 የእኔ የኑሮ ርዕዮተ ዓለም የአሳማ ነዉ፡፡ ሀፍተ ሥጋ ወዳድ ነኝ፡፡ ለነገሩ የእኔ ኑሮ ሥጋ ለሥጋ አይነት ነዉ፡፡ እናም በልቼ እንዳድር ያበቃኝን ሥጋዬን ማዋደዴ የሚያስደንቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዉበቴ እስካልረገፈ ድረስ በልቼ ማደር እችላለሁ፡፡ የሕይወት ርዕዮተ ዓለሜን ሌሎች አያዉቁትም፡፡ ቢያዉቁት ምናልባት ይሳለቁብኝ ይሆናል፡፡ እኔ ግን ለለግጣቸዉ ቁብም የለኝ፡፡ ስለ ነገ ለምን ልጨነቅ? ደግሞስ በሰቀቀን የተቀበልነዉ ትናንት እንደ ጥላ እንደዘበት ሲያልፍ አልታዘብንም? ታዲያ ነገ ምኑ ያጓጓል? ከድካም በቀር ከትናንት ኑረት ምን አተረፍኩ? መጪዉ ጊዜ ከኖርኩት ትናንት የተለዬ ሊሆን ይችላል?  

ባልኮኒዉን ከበዉ ቢራ የሚጨልጡት ጋለሞታ የሥራ ባልደረቦቼ ሳቅና ንትርክ አለሁበት ድረስ ይሰማል፡፡ ያዉ እንደ ለመዱት ሰዉ እያሙ ይሆናል፡፡ የቡና ቤት ሴት እንደ ሀሜት ከልቧ የምትወደዉ ነገር የለም፡፡ አብዛኛዉ የቡና ቤት ወሬ በግለሰቦች ታሪክ ላይ የሚሽከረከር ነዉ፡፡ መነሻዉም መድረሻዉም የሌሎች የተሸሸገ ጀርባ ነዉ፡፡ የሌሎችን የተሸሸገ የጀርባ ታሪክ የመቅደዱ ሂደት ተወዳጅ የሆነዉ ሁሉም የወሬ ኤክስፐርት፣ የወሬ ፕሮፌሰር የገዛ ሕይወቱን በከፊልም ቢሆን ተፅፎ ስለሚያገኝበት ነዉ፤ ስለሌሎች ማዉራት ስለራስ መስማትም ጭምር በመሆኑ ነዉ፡፡
ማኅበራዊ መስተጋብሬ ሰፊ ቢሆንም አንደበተ ቁጥብ ነኝ፡፡ በእዚህም ምክንያት አንዳንዶች ጋግርታም ናት ይሉኛል፡፡ ዝምታዬ ማንነቴን የጋረድኩበት ጭንብል ነዉ፡፡ ምስጢሬን በልቤ እቀብራለሁ እንጂ ለሌሎች አልነዛም፣ ወዳጆቼ እንኳ ልቤን አያዉቁትም፡፡ ጭንብሌ ቢገፈፍ የሚገለጠዉ ግብዝነቴ፣ ቂመኛነቴ፣ ከሀዲነቴ፣ ራስ ወዳድነቴ፣ ቅናቴ፣ ሀኬተኛነቴ፣ ጨካኝነቴ እና ሴሰኛነቴ ነዉ፡፡ አንደበተ ቁጥብነቴ ስሜ በሌሎች እንዳይጠለሽ የጋረደ ግምጃዬ ነዉ፣ በሐሜት ከመብጠልጠል የሚተርፍ ሰዉ ባይኖርም፡፡ ክፉም ሆንክ ደግ በሌለህበት እንደ ሙዳ ሥጋ ትቦጨቃለህ፣ እንደ ቋንጣ ትዘለዘላለህ፡፡ ቢሆንም ግን ቁጥብነትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ወዳጅ አገኘሁ ብሎ ለባዕድ ገመናን ገልጦ መንዛት አይገባም፡፡ ቀንደኛ ጠላቶቻችን ትናንት አብረዉን የበሉ አይደሉምን? መቃብራችንን ለመማስ የሚማስኑት የአሟሟታችንን መንገድ ስለሚያዉቁት አይደለምን? የዉድቀታችንን ፈለግ? የዛሬ ወዳጆቻችን ነገ ሲክዱን ጠልፈዉ የሚጥሉን በሽንቁራችን ገብተዉ ነዉ፡፡ 

ቡና ቤቱ ዉስጥ ከሚሠሩ ሴቶች በንፅፅር ያልጠለሸ ስም ያለኝ እኔ ነኝ፣ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ቢሆንም፡፡ ላይ ላዩን ሐሜትን የምፀየፍ ልምሰል እንጂ የሰዎችን ጀርባ መበርበር እወዳለሁ፡፡ አንዱ የሌላዉን ምስጢር እንዲዘከዝክልኝ ማድረጉም ለእኔ ተራ ተክህኖ ነዉ፡፡ የሌሎችን ጀርባ የማወቅ ጉጉት የሌለኝ ዳተኛ መስዬ ብታይም፣ ማን ምን እንደሆነ፣ ምን እንዳደረገ፣ ምን እንደሚፈልግ ልቅም አድርጌ አዉቃለሁ፡፡ ለምሳሌ፣ አዜብ ለጋስ ብትሆንም ከእኔ የባሰች በካና ናት፡፡ ቂልነቷ የበዛ ነዉ፣ ወርቅ ላበደረ ወርቅ የምትል ናት፡፡ ማሕሌት (ቅፅል ስሟ ቲና) የታወቀች ሐሜተኛ ናት፡፡ መክሊት የረባ ያልረባዉ ነገር ቶሎ የሚያስከፋት ሆደባሻ ናት፤ የመከዳት ታሪኳን ምሬት ጆሮ ለሰጣት ሁሉ በመዘክዘክ የምታሰለች ችኮ፡፡ ባመነዉ ያልተከዳ ማን ነዉ? ሄለን (ቅፅል ስሟ ሊሊ) አዱኛ አምላኪ ናት፣ ወዳጅነትን የምትሰፍረዉ በጥቅም ሚዛን ነዉ፡፡ ርዕዮቷ የተገነባዉ “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” በሚለዉ ብሂል ነዉ፡፡

#Inbox @Faraw_sam

#share @ethio_fiction