Get Mystery Box with random crypto!

#ርዕስ:- “እነ እሙጢ ጋ እየሄድኩኝ ነው” #ደራሲ:- ሌሊሳ ግርማ #የመጨረሻ_ክፍል ለመድረስ | ልብወለድ Ethio_Fiction

#ርዕስ:- “እነ እሙጢ ጋ እየሄድኩኝ ነው”

#ደራሲ:- ሌሊሳ ግርማ

#የመጨረሻ_ክፍል

ለመድረስ ብዙ ይቀራቸዋል። ሃያ ሁለት መጀመሪያ… ከዛ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሆስፒታል ቁልቁል ወደ ሀያ አራት…።
በእሷ በኩል እንጂ በስልክ በሚያናግራት ወንድ በኩል ለለቅሶዋ ምን ምላሽ እንደቀረበ መስማት አይችልም። ጥቅሉ ነገር ይገባዋል። ጥቅሉ ነገር ልጁን  ይዛባት እሙጢ ጋ እንድትሄድ አለመፈለጉ ብቻ ነው፡፡ ለማባበያ ምን አይነት ምክንያት እንደደረደረ ወይንም የተጠቀመው ብልሀት አድብቶ ለሚያደምጠው ሾፌር ባይገለጥለትም… የእናትየዋን የጉዞ  አቅጣጫ ግን ሊለውጠው አልቻለም፡፡   
“ወደመጣንበት ልመለስ…” ብሎ መጠየቅ የእርጎ ዝንብነት ነው። በራሱ ጭንቅላት በሰራው ካርታ እነ እሙጢ የሚወክሉት የቀድሞ ህይወቷን ነው። ሲ.ኤም.ሲ የሚባል የሀብታም ሰፈር ልጅ ታቅፋ ከመቀመጧ በፊት ለምዳ የኖረችውን የቀድሞ ታሪኳን--- አለባበሷን አልቀየረውም፤ አዲሱ ህይወቷ፡፡ በጉዞ ለመመለስ የተሳፈረችበት አቅጣጫ በምትሰማው ሙዚቃ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ሾፌሩን ታየው።

የልጁ አባት ላይ በስልክ አልጮኸችም። ወቀሰችው እንጂ አልኮነነችውም።  የደወለው አባትዬው መሆኑ እርግጥ ነው። በስራ ምክንያት ራቅ ያለ ይመስላል፡፡ የመሰለ ሁሉ ግን ነው ማለት አይቻልም፡፡ በስሜቱ ማሰብ ከጀመረ በቀላሉ ሊጭበረበር እንደሚችል ሹፌሩን ታሰበው፡፡
መዳረሻው የሆነ የሴተኛ አዳሪዋን መንደር ማታ ማታ ለመበጥበጥ ጮሆ የሚነሳ፣ ቀን ቀን ድምፁን አጥፍቶ በሩን ቆልፎ የሚሰወር አንድ ቤት ሊሆን ይችላል። በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ወደ ታች መውረድ ሲጀምሩ፣ “በዚህ ግባ” ብላ ቅያስ አሳየችው። በውስጥ ልትንሸራሸር ፈልጋ እንጂ መልሰው ሲወጡ መደበኛውን የሀያ ሁለት ቦሌ መንገድ ያዙ።

መልሳ እነዛኑ የድምፅ ሀጢአት ዘፈኖችን ከፍታለች። በውስጥ መንገድ ከተንሸራሸሩ በኋላ የተበጠበጠው መንፈሷ ረግቷል፡፡ ሀቅታው፤ ስቅታው ቆሟል። መጠነ ቁራጭ ወጥቶላታል። ሾፌሩ ሊጠይቃት አልፈለገም። በጥቅሉ የሚሰማው የጉዳዩ አሳዛኝነት በዝርዝሩ ውስጥ ተራ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ የተሰማውን ርህራሄ በግዴለሽነት ለብጦ ዝም ማለት ተሻለው፡፡
“ውይ ትራፊኩ እንዳይቀጣህ” ብላ በርህራሄ እጇን በደረቷ ላይ ጫነች። ቀጥሎ ደግሞ “እንዴት ትራፊክ እፈራለሁ መሰለህ!” ብላ እጇን ትከሻው ላይ ሳታስበው አሳረፈች። መስላ የምትታየውን እንዳልሆነች ያለ አንደበት መሰከረለት። በእጇ ንክኪ ውስጥ ባገኘው መልዕክት እርግጠኛ ሆነ። ቢያንስ ባል አላት ብሎ ትንሽ ከፍታ ሰጣት። መጀመሪያም ያልሆነችውን አባዝቶ ነበር የኮነናት። ወዲያው አሁን ደግሞ ትንንሽ ብልጭታዎችን አጋኖ ሊያዳንቃት ፈልጓል፡፡