Get Mystery Box with random crypto!

የቀጠለ... አንድ ቅርጫት ሙሉ ሎሚ የያዘ ሻጭ መጥቶ ቁጭ ከማለቱ ህዝበ ሠራዊት፤ ልቡ በፍቅር የነ | ልብወለድ Ethio_Fiction

የቀጠለ...
አንድ ቅርጫት ሙሉ ሎሚ የያዘ ሻጭ መጥቶ ቁጭ ከማለቱ ህዝበ ሠራዊት፤ ልቡ በፍቅር የነደደ፤ቀልቡ በሎሚ መጥፋት አብሮ የጠፋ፤ ይሉኝታ ሳይዘው ሎሚ ሻጩን ከበበው፤ኧረ ሰፈረበት ማለት ይቻላል፡፡
አንድ ሎሚ አንድ ብር! (አንድ ብር ለአንድ ወገን እንዳበልቃ፣)
ማን ይከራከራል! ፣ ወጣ ከፈል! ፣ ቀበል ሸተት!
አሸት!
ወርወር ባየር!
ቀለብ!!
ባይን ተፈቃሪን መመልከት፤ሎሚ ብወረውር ..አሀ አሀ አሀ… እያሉ፡፡

አፍቃሪው ግፊያውን አልቻለውም፡፡ ወትሮም ቢሆን ይሉኝታ ያጠቃዋል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ አንድ ጥቅሻ ስንት ተአምር በሚፈጥርበት ዘመን ፍቅሩን ለመግለጽ የሎሚ ግፊያ ፍቅር ያዛከረውን ልቡን አያጠፋውም ነበር፡፡ እናም በይሉኝታ ደርቆ እንደቆመ አንድ ቅርጫት ሎሚ በአይኑ ስር ተሸጦ አለቀ፡፡በመጨረሻም የቅርጫቱ ቂጥ ቀዳዳ ውስጥ አንድ የደረቀ ሎሚ ተገኘ፡፡ ሎሚ ሻጩ የአፍቃሪውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም የሎሚውን ወቅታዊ ሁኔታ በመገምገም በሀምሳ ሳንቲም ሸጠለት፡፡

አፍቃሪው ሎሚውን አሸት- አሸት ለማድረግ ሲሞክር ከረረበት ግን ያለው አማራጭ እሱው ብቻ በመሆ ደረቁን ሎሚ እያሸተተ የዐይን ፍቅረኛውን አሰሳ ገባ እያንጎራጎረ…

ሎሚ ብወረውር ..አሀ አሀ አሀ…
ደረቷን መታኋት..አሀ አሀ አሀ…
አወይ ኩላሊቷን..አሀ አሀ አሀ…
ልቧን ባገኘኃት ..አሀ አሀ አሀ…

አለቻ ኩላሊት!

ፍቅርና ኩላሊትን በዘፈን ያገናኘ አምላክ ተፈቃሪዋን እፊቱ አመጣለታ! በዘመናዊ ስፌት የተሰፋ ነጭ የሀገር ልብስ ለብሳለች፡፡ ቀሚሱ ከላይ ባለማንገቻ ሆኖ ደረቷ ሎሚውን እንደ ካሜሩን ኳስ ተጫዋች ለማብረድ ይመስላል ወለል ብሎ ተጋልጧል፡፡

‹‹ይኼው ደረትሽ ነው ያጣላኝ ሁሉን፤

እስቲ ሸፈን አርጊው ያጡት እንደሆን?››

የሚለው ዘፈን በሀሳቡ ውልብ አለበት፡፡ መችስ ፍቅር የነደፈው ሰው ካለ ዘፈን ማርከሻ የለው፡፡

ሆነም!

ተፈቃሪዋ ጠጉሯ ላይ ባለባንዲራ የአንገት ልብስ ሸብ አድርጋ ባህላዊ ዘፈን ከሚያጅቡት ሰዎች ጋር ከዳር ቁማ ታጨበጭባለች፡፡

አያት፤ ጮክ ብሎ አያት!

አየችው፤ አይኗን ሰበር አድርጋ፡፡

የምታውቀው መሰላት፤ ነገር ግን ዛሬ ወንዱ ሁሉ <<ለጥምቀት ያልተጠበሰች ሴት…›› ብሎ ቆርጦ የተነሳ ይመስል አይኑ ተጎልጉሎ እንደታቦታቱ ውጪ እስቲያድር ድረስ ስለሚያፈጥ ብሶት ከወለዳቸው አንዱ አድርጋ ነው የቆጠረችው ግን አሁንም ያያታል፡፡ ሰረቅ አድርጋ አየችው፡፡

ተጠጋት!

ምንም ሳያናግራት በሎሚው ደረቷን መታት!
በቁሟ ዥው ብላ ወደቀች፡፡

በዙሪያዋ ያሉ የሚያውቋትም፤ የማያውቋትም ሰዎች ተጯጯሁ፤
ተዝለፈለፈች፤ ጥምቀታውያን ከበቧት…

‹‹ያዙት!››
‹‹ያዙት!››
‹‹ ያ ነው ያዙት! ፤‹‹ያዙት!›› ተባባሉ
‹‹በምንድን ነው የመታት?››
‹‹በጩቤ ነው መሰለኝ የወጋት!›› አለ ወደቀ ሲሉት ተሰበረ ለማለት የማይመለሰው ጥምቀታዊ
‹‹ኧረ እባካችሁ ሰይጣን ሳይሆ አይቀርም?››
‹‹ ያዙት! ፤‹‹ያዙት!››

አፍቃሪው ግን አልሮጠም፤ ስልታዊ ማፈግፈግ ለማድረግ አሰበ ... መልሶ ተወው።

‹‹ኧረ ልብ ድካም ሊሆን ይችላል›› ትላለች ሌላዋ ነገር እንደውሃ የጠማት ጥምቀቴ፡፡

‹‹የሚጥል በሽታ ሳይሆን አይቀርም እስቲ ክብሪት አምጡ›› ይላል ሌላው የሀበሻ መድሃኒት አዋቂ መሳይ፡፡

አፍቃሪው አሁንም በላብ ተጠምቆ ፈዞ እንደቆመ ነው፡፡

‹‹የታለ ወንጀለኛው?›› አሉ ሰው ለማሰር የቸኮሉ የሚስሉ ታጣቂዎች

‹‹ያውና! ያውና!›› ልክ ፈሪሳውያን ጌታን አሳልፈው እንደሰጡት ከባቢዎቹ እጃቸውን ወደ አፍቃሪው ቀስረው ዋልያው ጎል እንደገባ ሁሉ በአንድ ድምፅ ጮኹ!
ፈዞ ቆሟል -አፍቃሪው፡፡

‹‹ምን አልባት ተለክፋ ሊሆን ስለሚችል ወደጠበሉ ውሰዷት›› አሉ ድምፃቸው በአዶከበሬ ጭፈራ የተዘጋ ውቃቢያም የሚስሉ ጎፈሬ ባልቴት፡፡

የቀይመስቀል አንቡላስ ደርሶ ተፈቃሪዋን ጭኖ እሪሪሪሪሪሪ እያለ ነጎደ፡፡

የፖሊስ መኪና መጣ፡፡

‹‹ኧረ ሎሚ ነው የወረወርሁት፤ ሎሚው ደረቅ ስለሆ ነው…›› ለማስረዳት ሞከረ አፍቃሪው፤

‹‹ እሱን ጣቢያ ስትደርስ ታስረዳለህ፤ የምትናገረው እያንዳዱ ነገር በራስህ ላይ ሊመጣ ስሚለሚችል እስክትጠየቅ ድረስ ዝም እንድትል ትመከራለህ!›› አለው አማርኛ የእናቱ ምላስ የማይመስለው ፖሊስ፡፡

‹‹ሎሚው ደረቅ… ››

‹‹ሰውዬ ዝም በል! ››

"‹‹ሎሚ ሳልወረውር አሀ- አሀ…

ምነው በቀረብኝ አሀ- አሀ…

እንኳንስ ስድስት ወር አሀ- አሀ…

ዓመት ባፈቀርኩኝ አሀ- አሀ…"

እያለ በውስጡ እያንጎራጎረ አፍቃሪው ዝም ብሎ ተቀመጠ፤ የፖሊስ መኪናው በጩኽት ጃንሜዳን ለሁት ከፍሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተፈተለከ፡፡

ተፈጸመ!

contact :- @sam_lizu

share @ethio_fiction