Get Mystery Box with random crypto!

ርዕስ :- ሎሚ ብወረውር! አዘጋጅ :- ሳሚ ሊዙ የዘገሊላ ዕለት ነይልኝ በኔ ሞት ላስተርዮ ማርያ | ልብወለድ Ethio_Fiction

ርዕስ :- ሎሚ ብወረውር!
አዘጋጅ :- ሳሚ ሊዙ

የዘገሊላ ዕለት ነይልኝ በኔ ሞት
ላስተርዮ ማርያም እመጣለሁ እኔም
.... ሰሞኑን ባፍቃሪው ምናብ ውስጥ የሚመላለሰው ዜማ ይኼው ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ራሱ ለስንተኛ ጊዜ በውስጡ እንዳንጎራጎረው የሚያውቁት እሱና ልቡ ብቻ ናቸው፡፡ ተፈቃሪዋን አይቶ ከወደዳት ከሐምሌ አቦ ጀምሮ እስከዛሬው የጥምቀት በዓል ድረስ ድፍን ስድስት ወር ከማየት በቀር አንድም ቀን ማፍቀሩን አልገለጸላትም፡፡ ደብዳቤ እንዳይጽፍ ቃላት ሸሹት፤ አማላጅም ለመላክ ድፍረቱን አላገኘም፡፡ ዛሬ ግን ጥምቀት ነው ሎሚ ወርውሮ ቁርጡን ለማወቅ ቆርጧል

‹‹መቀስ የት ይገኛል ቁርጥ ነው ዘንድሮ!››

"ሎሚ ብወረውር ..አሀ አሀ አሀ…
ደረቱን መታሁት..አሀ አሀ አሀ…
አወይ ኩላሊቱን..አሀ አሀ አሀ…
ልቡን ባገኘሁት ..አሀ አሀ አሀ…"
ይለዋል፡፡ የዘነበች- ጭራ ቀረሸን ዘመን የተሻገረ ዜማ፤ ለራሱ እንዲመቸው እያስተካከለ፡፡

የሰፈራቸው የየካ ሚካኤል ታቦት ወደ ደብሩ የሚገባው በጥምቀት ማግስት በመሆኑ፤ የጥምቀት ዉሏቸው ጃን ሜዳ እንደሚሆን ተፈቃሪዋ ከባልንጀሮቿ ጋር ታቦት እየሸኙ ሲመካከሩ ሰምቷል፡፡

ለጥምቀት መንገዶች ሁሉ ወደ ጃን ሜዳ ያመራሉ፤ ምክናያታቸው የነፍስም የሥጋም ነው፡፡ ገሚሱ ሀይማኖታዊ፤ ገሚሱ በህላዊ፤ ዘመናዊ ወይም ፍቅራዊ ሊሆንም ይችላል፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባህር እንደተጠመቀው ሀጢያታቸውን በጃን ሜዳ ጠበል አጥበው ለማንጻት እንደተቃጠለ ቤት ጠበል በጎማ ሊረጩ ጃን ሜዳ የሚገኙ እንዳሉ ሁሉ፤ ድምጼ እስቲዘጋ እዘፍናለሁ ብለውየ ተሳሉ ጎልማሶች የአገር ባህል ልብሳቸውን እንደለበሱ የማንንም ልብ የሚያማልለውን ባህላዊ ዘፈን ያንቆረቁሩታል፤ ወላ ባላገሩ፤ ወላ ኢትዮጵያን አይዶል ሳይሉ፡፡ ዘመናዊዎቹ ደግሞ በሀርሞኒካ …

 ‹‹ዲ- ዲ- ዲሪሪሪ- ዲዲ ዲሪሪ- ዲዲ …
ፒፒፒሪሪሪሪ ጲርጲርጲርርርር">>
ሳብ አርግና ወደዚህ አምጣት፤እምቢ ካለች፤ በጊዜ ተዋት..›› ይላሉ እዚህም እዛም፡፡
ምስኪኑ አፍቃሪው ደግሞ ሎሚ ይፈልጋል፡፡

አሁን እስቲ ማን ይሙት ሎሚ በአገር ይጠፋል ብሎ የሚያስብ አለ?፣ ፍቅር ተቀስቅሶ፤ የሚያፈቅር ሞልቶ፤! የምትፈቀረዋ ተመርጣ፤ሎሚ ለሽታ እንኳን አይጠፋ መሰላችሁ? አፍቃሪው ከየካ ሲነሳ እዚህ ከምገዛ እንዳይጠወልግብኝ ከዚያው እገዛዋለሁ ብሎ ችላ ብሎት መውጣት፡፡ ጃን ሜዳና አካባቢው ደግሞ ያለወትሮው አንድም ሎሚ የያዘ ነጋዴ ጥፍት! መቼም ነጋዴን ነጋዴ አያጣውም ብሎ በማሰብ ተመሳሳዩን ብርቱካን የሚሸጠውን ልጅ-እግር ነጋዴ፤

‹‹ስማ የኔ ወንድም ሎሚ የሚሸጥ የለም እንዴ?››
‹‹ሎሚ ስለጠፋ በአሁኑ ጊዜ አይገኝም›› ብሎ ሳይጨርስ ነጋዴው

‹‹ኤክስፖርት ይደረጋል እንዴ?›› ጠየቀ አፍቃሪው ሰግቶ

‹‹ፍሬንድ እዚህ አገር ዕቃ ሲገባ እንጂ ወደ ውጪ ሲወጣ የምናውቀው ቡና ብቻ ነበር እሱም እየተንገዳደገደ ነው፡፡›› ለማንኛውም ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስ፤ ቅድም አንድ ልጅ ቅርጫት ሙሉ ሎሚ በአንድ ብር በአምስት ደቂቃ ሸጦ ጨርሷል፤ ምን አልባት ሌላ ይመጣ ይሆናል ጠብቅ፡፡›› ዛሬ መቼስ ሎሚ ብወረውር ..አሀ አሀ አሀ… አይደል፣ ብሎት በዜማ ወደ ስራው ተመለሰ፡፡

አፍቃሪው ጠበቀ

ረዥም ሰዓት ቆመ

ሎሚ የውሃ ሽታ ሆነ፡፡

በዚህ ጊዜ የአፍቃሪውን መጨነቅ የተረዳው ብርቱካን ነጋዴ፤ ‹‹ባባዬ ሎሚ የምትመስል ብርቱካን ልምረጥልሽ እንዴ?›› አለው፡፡ አፍቃሪው በግድ ሳቀ ‹‹ወዶ አይስቁ አሉ፡፡›› በፍቅር ኮሜዲ የተሰላቹ አበሾች፡፡

‹‹…ብርቱካን በልቼ፤ሎሚ ሎሚ አገሳኝ
ብርቱካኔ…
አንቺ እንደምን አለሽ፣
እኔን ጤና ነሳኝ
አንቺ እንደምን አለሽ፣
እኔን ጤና ነሳኝ፡፡››
እያለ አፍቃሪው ከሎሚ ሳይርቅ ቅኝቱን ቀይሮ በለሆሳስ ማንጎራጎሩን ተያያያዘው፡፡

ሆነም!