2023-04-20 16:30:37
በመዲናዋ ከ1.5 ቢልየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው "ስቴይ ኢዚ ፕላስ" ሆቴል ወደ ሥራ ሊገባ ነው
በአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ ቶታል አካባቢ ከአንድ ነጥብ 5 ቢልየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው፤ "ስቴይ ኢዚ ፕላስ" ሆቴል ከኹለት ሳምንታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለጸ።
በጥንዶቹ ዳግማዊ መኮንን እና ህይወት አየለ ባለቤትነት የተገነባው ሆቴሉ፤ በባለፉት ስምንት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረ ሲሆን፤ ምድሩን ጨምሮ ዘጠኝ ወለሎች አሉት።
ሆቴሉ ባለ አምሰት ኮከብ ደረጃ ለማግኘት ማመልከቱን የገለጹት የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አሚር ሰይድ፤ በአጠቃላይ 103 ክፍሎች፣ ከ15 እስከ 1 ሺሕ 500 ሰው ማስተናገድ የሚችሉ 6 የስብስባና የሰርግ አዳራሾች እንዲሁም፤ የጥበብና ቲያትሪካል አርት እና ሌሎች ዝግጅቶችን ማቅረብ የሚያስችሉ ምቹ አዳራሾችም እንዳሉት ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሦስት ባር እና አንድ መመገቢያ አዳራሾች ያለውና እራሱን የቻለ የዳቦና የኬክ ጋሪያ ኪችን ያለው ሲሆን፤ በሰዓት ከ30 ሺሕ በላይ ዳቦዎች ማምረት የሚችል ማሽን፣ ኦፕን ኪችን እንዲሁም ግዙፍ የላውንደሪ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ማሽኖች እንደተገጠሙለትም አሚር ጨምረው ገልጸዋል።
የሆቴሉ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ህይወት አየለ በበኩላቸው፤ ሆቴሉ ከእንጦጦ ፓርክ እና ቦታኒክ ጋርደን ለሚጡ ጉብኚዎች እንዲሁም፤ በእንጦጦ እና ሱልልታ የሩጫ ልምምድ ለሚያደርጉ አትሌቶች በቅርብ የሚገኝ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል መሆኑን በመግለጽ፤ መኝታ ክፍል ለያዘ እንግዳ ሙሉ በሙሉ አዲስ አበባን ከአራቱም አቅጣጫ መመልከት የሚያስችል ልዩ እይታ እንዳለውም አስረድተዋል።
ሆቴሉ በአጠቃላይ የያዘው ስፍራ 2,250 ሜትር ስኬር ሲሆን፤ በ 1,700 ስኬር ላይ ሆቴሉ መገንባቱንም ህይወት ጨምረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሆቴሉ ባዘጋጀው ከመቶ መኪናዎች በላይ ማስተናገድ በሚችለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ፤ የኤሌትሪክ መኪና ይዘው ለሚመጡ ደንበኞቹ ኤሌትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታም አዘጋጅቷል።
በቅርቡ በሚጠናቀቁት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ስፖርት መስሪያ ጂም፣ የሴትና የወንድ ሳውና እና ስቲም ባዝ፣ መዋኛ ገንዳ፣ የዮጋ አዳራሽ እንዲሁም የባህል ሬስቶራንትና የመዚቃ አዳራሽ እንደሚኖረው ተገልጿል።
"ስቴይ ኢዚ ፕላስ" ሆቴል በሰከንድ አምስት ሊትር ውሃ ማመንጨት የሚችል የራሱ የከርሰምድር ወሃ ያለው ሲሆን፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ 24 ነፃ የውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል።
ሆቴሉ በአጠቃላይ ከ 250 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉም ተነግሯል።
Via አዲስ ማለዳ
@etconp
509 viewsItoophiyaa , 13:30