Get Mystery Box with random crypto!

የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የሴቶች የጅምላ ምልመላ ያሳስበናል አሉ የ | ሰበር ዜና ET🇪🇹

የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የሴቶች የጅምላ ምልመላ ያሳስበናል አሉ
የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች የሳውዲ አረቢያን ደካማ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው የሴት ሠራተኞች የጅምላ ምልመላ ያሳስበናል ሲሉ ገለጹ፡፡

አሁንም ቢሆን በርካታ ስደተኛ ሠራተኞች በሳውዲ አረቢያ ከሠራተኛ ሕጎች የተገለሉና በዘመናዊ ባርነት ስርዓት ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው ተብሏል፡፡

<ካፋላ> በተሰኘው ስርዓት አንድ ሠራተኛ በደል ቢደርስባት እና ከአሠሪዎቿ ብትሸሽ ፓስፖርቷን ጨምሮ የተለያዩ የሰነድ መረጃዎቿን እንድታጣ እንደሚደረግ እና ይህ ስርዓት አሁንም ለውጥ እንዳልተደረገበት ነው የተገለጸው፡፡

‹‹ሳውዲ አረቢያ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በዘፈቀደ በማሰር እና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ለእንግልትና ለሞት በመዳረግ፤ ሌሎችንም በመደብደብ ከአገሯ እንዲወጡ አድርጋለች›› ሲሉ የስደተኞች መብት ተመራማሪ ናድያ ሃርድማን ለአልጀዚራ አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያ ይህን ዓይነት አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ወደለባት ሳውዲ አረቢያ 500 ሺሕ ሴት ሠራተኞችን ለመላክ ማቀዷን የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎቹ ኮንነዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የሚላኩት ሴት ሠራተኞች ከሳውዲ አረቢያ የሠራተኛ ጥበቃ ሕጎች የተገለሉ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ለሚደርስባቸው በደልም ምንም ዓይነት ሕጋዊ መፍትሔ የሌላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራተኞችን ለተሳዳቢ አሠሪዎች አሳልፎ የሚሰጠውን የካፋላ ስርዓትን ማፍረስን ጨምሮ ሙሉ ጥበቃን ለማረጋገጥ መፍትሔ መፈለግ አለበት ያሉት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች፣ በውሸት የጥበቃና ዋስትና ከለላ ሴቶችን ወደ ስደት መገፋፋት የለበትም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በዘንድሮው በጀት ዓመት የ500 ሺሕ ሴቶችን የጉዞ ወጪ ችሎ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመላክ ሥልጠና በመስጠት ላይ ሲሆን፣ የመጀምሪያ ተጓዦች ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ላይ መጓዛቸው ተመላክቷል፡፡

በ266 ዶላር ወርሃዊ ክፍያ ለቤት ሠራተኝነት የሚሄዱት የኢትዮጵያ ሴቶች፣ ከ18 እስከ 40 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ የኮሌጅና የዩንቨርሲቲ ምሩቃንንም ያካተተ ነው፡፡

ሠልጣኞች ከመንግሥት በኩል እድሉ ሊያመልጣቸው የማይገባ የሕይወት ዘመን ወርቃማ እድል ነው መባላቸውን ገልጸዋል፡፡

በፈርንጆች 2020 የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ስቃይና መገደል ካረጋገጠ በኋላ የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያወግዝ ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡
አዲስ ማለዳ

@ET_SEBER_ZENA
@ET_SEBER_ZENA