Get Mystery Box with random crypto!

አንዱዓለም አራጌ እና ኢዜማ ተለያዩ ለ ኢዜማ የአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 12/13 ሊቀመንበር አዲ | ሰበር ዜና ET🇪🇹

አንዱዓለም አራጌ እና ኢዜማ ተለያዩ
ለ ኢዜማ የአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 12/13 ሊቀመንበር አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- ከአባልነት መልቀቅን ስለማሳወቅ፦

ክቡርነትዎ እንደሚገነዘቡት፣ በኢትዮጵያ ረጅም የህላዊ ዘመን ውስጥ በፓለቲካ ሰማያችን ላይ የደቀደቀውን የሚዳሰስ የአገዛዝ ጨለማ ለመግፈፍ የማያልቁ የሚመስሉ ረጃጅም የመከራ ሌሊቶችን ብናሳልፍም፣ ይልቁንም ጨለማው በርትቶ የነፃነት ጀምበርም ከአድማሳችን እጅግ ርቃ በጭቆና ጥቀርሻ መቀበሯ ጥልቅ ህመም ቢፈጥርብን፤ ለሀገራችን የንጋት ኮኮብ ሆኖ፣ ሕዝባችንንም ከአገዛዝ ቀምበር አላቆ በፍቅር፤ በፍትህና በወንድማማችነት ኮረብታዎች ላይ ግዘፍ ነስታ የምትቆም፣ ያለፉትንም የሃሩር ዘመናት የምታስረሳ ኢትዮጵያ እንድትጠባ ከልብ በመሻት ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ን መመስረታችን ይታወቃል።

እኔም ኢዜማን ከመጠንሰስ እስከ መመሥረት፣ ከምሥረታ በኋላም ወረዳችንን በአባልነት ፓርቲያችንን በአመራርነት እስከማገልገል የዘለቀ አቅም የፈቀደውን እንቅስቃሴ ማድረጌም ይታወሳል። የቆዩ ስህተቶችን በፓርቲያችን ውስጥ ላለመድገሞ እንዲሁም የህልሞቻችን ሁሉ በኩር የሆነውን ሰብዓዊ ልእልና የነገሠባት ኢትዮጵያን በእርግጠኝነት እውን ለማድረግ በሰከነና በተጠና መንገድ ለመራመድ ከፍ ያለ ጥረት ስናደርግ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአጋዛዝ ውስጥ ተወልዶ በአገዛዝ መዳፍ ውስጥ እንደ ሸበተ ትውልድ እፍኛችንን የሞላው ጉም ነው ወይንስ የሚጨበጥ ተስፋ የሚለውን ጉዳይ ለመገምገም ፈፅሞ በዚያ መጠን መቸገር ሳይገባን አላስፈላጊ የህልም ሩጫ የሚመሰሉ የሃሳብ ልፊያዎችን ለማድረግ ተገደን ቆይተናል፡፡

ሁኔታዎችን በውይይትና በሀሳብ ፍጭት ለመፍታት መሥራቱ የሚከበርና እንደ ፖለቲካ ባህልም ልናዳብረው የሚገባ መሆኑ እሙን ነው፡፡ይሁን እንጂ ምንም እንኳን በጭንቅም ቢሆን ዛሬ ላይ ቆመን በምልሰት የክርክሮቻችን መቋጫና ውጤቱም ምን እንደሆነ እያየን ቢሆንም፣ በወቅቱ አንኳር በሚሰኙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በድምፅ ለመሸናናፍ ያደርግናቸው እልህ አስጨራሽ ፍልሚያዎች የፓርቲው አዎንታዊ መገለጫዎች ናቸው ብዬ እወስዳለሁ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሁሉ መድህን ለመሆን ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በተገኙ አባላት የተመሰረተ ፓርቲ ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ ድርሳን ላይ ከሰፈረው መከራዋ ሁሉ የከፋውን በምታስተናግድበት በዚህ ዘመን፣ የክብር ፈርጦቿ ሲረግፉና ፀንታ የቆመችባቸው አምዶች በአገዛዝ መዶሻ ሲፈረካከሱ፤ የተለያዩ የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ፤ ታግሎ ሕዝቡን በማታገል ከደመና በላይ አንገታቸውንና ልባቸውን አደንድነው፣ በፈርዖን ሰረገላ ላይ ተዘልለው ፣ ሕዝቡን ወደ ቀይ ባህር ዳርቻ በማሳደድ ሀቅላቸውን የሳቱ ገዢዎች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ እና ለሁላችንም ድህነት ይሆን ዘንድ መሥራት ቢጠበቅበትም ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ሆኖ የተሳከረ ሚና በመጫወት እየተንጎላጀ ይገኛል ።

እኛም እንዳቀድነው፣ ሕዝባችንም አብዝቶ እንደተመኘው፣ አገዛዝንና ከእርሱም የሚታጨደውን ሰቆቃ በማምከን በሀገራችን ሰማይ ሥር እውነተኛ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ይሰፍን ዘንድ አመርቂ የሚባል አስተዋፅኦ ለማድረግ አለመቻሉ እንዳለ ሆኖ፣ እንደ “የበዐል ነቢያት” አገዛዝን ከቦ እያሸበሽበ፣ የአገዛዝ ጡጫ እንዲፈረጥም ማድረጉ ለብዙዎች ፍች ያልተገኘለት ቅዠት ሆኖአል። ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ከስሁት መንገዱ ለመመለስ በማይችልበት መዳፍ ውስጥ መጨመቁ ነው። ያነሳኋቸውንና ነገሬን ላለማርዘም እንዲሁም ከተገቢነት አንፃር መዝኘ የተውኳቸውን ሀሳቦች ግንዛቤ ወስጥ በመክተት ደጋግሜ የሁኔታ ትንታኔ ብሰራም የኢዜማ ስብራት ሲጠገን ለማየት አልቻልኩም ። ለመላምታዊ ጥያቄዎቼም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ባለመቻሌም አዝናለሁ፡፡

ክቡርነተዎ እንደሚያውቁት፣ የፖለቲካው አውሎ ነፋስ ገና ከሩቅ ግሳንግሱን እየጠራረገ ሲመዘገዘግ፣ የለም የፓርቲያችንን ቁመናና አሰላለፍ ከወዲሁ እናስተካክል የሚል ተማጽኖ ከማቅረብም ባለፈ በአባላት ፊት ቀርቤ ብሞግትም የሚገባውን ድጋፍ ባለማግኘቴ ውሳኔያቸውን በጸጋ ተቀብዬ በአባልነት መቀጠሌ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍ ብዬ ካወሳኋቸው ምክንያቶችበተጨማሪ በእለት ከእለት ውሎዬ የማገኛቸው ዜጎች ሁሉ አሁንም የፓርቲው አመራር አባል እንደሆንኩ እንደሚቆጥሩ ለመገንዘብ ችዬአለሁ፡፡ በመሆኑም በሌለሁበት እርምጃ የውግዘትም ሆነ የውዳሴው ተቋዳሽ ለመሆን አልሻም። ስለሆነም ከዚህ በላይ ሳልዘገይ ነገሮች እንደየዘርፋቸው ማሰቀመጥ ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በሌላ በኩል እንደጠቀስኩት ኢዜማን አይነ -ግቡና ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ የሰነቅነው ህልም እውን ይሆናል ወይ? በሚለው ጉዳይ ላይ ደጋግሜ የሠራሁት የሁኔታ ትንታኔ አዎንታዊ ምላሽ ሊያስገኝልኝ ባልቻለበት ሁኔታ ኢዜማ ውስጥ መቀጠሉ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

በመሆኑም ይህን በመሰለ ሁኔታ ተጨማሪ ቀናትን በኢዜማ ጣራ ሥር መቀጠል የሚያስችለኝ አንዳች አይነት ምክንያት አልቀረኝም።ክቡርነተዎ ፈቃድዎ ቢሆን ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ በተለያዬ ደረጃ ለሚገኙ የኢዜማ ቤተሰቦች መልእክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ ፤ለተወደዳችሁ የኢዜማ አባላት፤ አብረን የተለምነው መንገድ የነጠረ የሚባል አይነት ቢሆንም ፤ ከስልት አንፃር የተከተልነው መሰመር እሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ እንዳደረገን በቀና ልቦና በሕዝባችን ዘንድ ያለንን ሥፍራ መረዳት ብቻ ብዙ ይናገራል፤ ሕዝብ ምን ፍሬ አለው ካላልን በስተቀር። በመሆኑም ብዙ ድንቅ የሚባሉ ጊዜዎችን አብረን ብናሳልፍም ከፍ ብዬ በገለፅኳቸው ምክንያቶች አብሬያችሁ ልጓዝ ባለመቻሌ በጣም አዝናለሁ! እዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ፈጽሞ ቀላል እንዳልነበረም ልገልፅላችሁ እወዳለሁ፡፡ከእናንተ ጋር ያሳለፍኳቸው ውስን የትግል አመታት በሕይወቴ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውና ሁልጌዜም አክብሮቴን የምቸራቸው እንደሆኑ እገልፅ ዘንድ ይገባኛል፡፡ እንዲሁም በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኜም ቢሆን ፣ ከልብ ባዘንኩባቸው ጊዜያትም እንኳን ሳይቀር ለእናንተ ያለኝ ፍቅር አለመቀየሩን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡

ፓርቲውን በሃላፊነት እንዳገለግል ለሰጣችሁኝ እድል፣ ላሳያችሁኝ ፍቅርና በጎነት ሁሉ ከልብ አመሠግናለሁ፡፡ አብረን ባሳለፍናቸው አመታት ቅር ያሰኘኋችሁ ወንድሞችና እህቶች ካላችሁ በዚህ አጋጣሚ ከልቤ ዝቅ ብዬ ይቅርታ ልጠይቃችሁ እወዳለሁ፡፡ የእኔ የሁኔታ ትንታኔ ስህተት ሆኖ ያቀዳችሁት ሁሉ ተሳክቶ ኢዜማም የእውነት ዘመን ተሻጋሪ፤ አይነ- ግቡና ለኢትዮጵያ ሕዝብም መድህን እንዲሆን የምታደርጉት ጥረት እንዲሳካ ከልብ እመኛለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በተለያየ መንገድ ፣ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ኢዜማን ስትደግፉ አብሬያችሁ ለመሥራት እድሉ ለገጠመኝ ለማከብራችሁና ለምወዳችሁ ወገኖቼ ሁሉ ከብዙዎቻችሁ ጋር ለመሥራት መቻሌን ከፈጣሪ እንደተቸረኝ ትልቅ ጸጋ እቆጥረዋለሁ፡፡ ምናልባትም ከእኔ ከዚህ በላይ ጠብቃችሁ የጎደለ ነገር ካለ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

በምርጫ ወረዳ 12/13 እንዲሁም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳይገባኝ ለለገሳችሁኝ ከፍ ያለ አክብሮትና ፍቅር ከልብ እያመሰገንኩ ፍቅርና አክበሮቴ እጥፍ ተባዝቶ ይድረሳችሁ! በተፈጠረው ሁኔታ ስለሚያድርባችሁ ቅሬታ ሁሉ ይቅርታ እየጠየቅኩ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ ለተሠሩ ግድፈቶች ሁሉ ሃላፊነት ለመዉሰድ ዝግጁ መሆኔን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

አንዱአለም አራጌ የኢዜማ የቀድሞ አባል
@ET_SEBER_ZENA
@ET_SEBER_ZENA