Get Mystery Box with random crypto!

በአማራ ክልል እየተፈፀሙ የሚገኙ ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በማስመልከት ከኢትዮጵያ እስልም | ESAT (ኢሳት🇪🇹)®

በአማራ ክልል እየተፈፀሙ የሚገኙ ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በማስመልከት ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተሠጠ መግለጫ

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በታጣቂዎች እየተፈፀሙ የሚገኙትን፣ በተለይ ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጋር በሚያደርገው የመረጃ ልውውጥ በቅርበት ሲከታተላቸው ቆይቷል። ጠቅላይ ምክር ቤታችን፣ ሁኔታዎች ከዛሬ ነገ ይሻሻላሉ በሚል ነገሩን በትዕግሥት ለመያዝ ቢሞክርም፣ ሁኔታዎቹ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ በመሄድ ላይ መኾናቸውን ለማወቅ ችለናል።

መጋቢት 29/2016 ምሽት የአማራ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ባህር ዳር ከተማ፣ ከቀበሌ 14 መስጂድ የመግሪብ ሰላታቸውን ሰግደው እየወጡ በነበሩ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት (አንድ አባትና ሦስት ልጆቻቸው) እንዲሁም ጎረቤታቸው የኾነ ሌላ አንድ ግለሰብ፣ በታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን በከባድ ሐዘን ነው የሰማነው:: በተመሳሳይም በሞጣ ከተማ በአንድ ምዕመን ላይ ግድያ መፈፀሙንና በጎንደር ከተማ ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙን፤ መስጅድን በጥይት መምታት ቦምብ መወርወር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተፈፀመ በመሆኑ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መጋቢት 30/2016 ባወጣው መግለጫ አሳውቆናል።

የግፍ ግድያው የተፈጸመባቸው የእነዚህ ምዕመናን ሥርዐተ-ቀብር በትናንትናው ዕለት ተፈጽሟል። አላህይዘንላቸው፤ ቤተሰቦቻቸውን መጽናናትን ይስጣቸው፡፡

በአማራ ክልል ሞጣ ከተማ ታጣቂዎች አንድን ወጣት ካገቱ በኋላ፣ ቤተሰቦቹን በማስፈራራት 300 ሺህ ተቀብለው ሲያበቁ ታጋቹን በጭካኔ መግደላቸውንም ከክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል::

በሁለቱ ከተሞች ከተፈጸሙት የግፍ ግድያዎች በተጨማሪ መጋቢት 26/2016 እንዲሁም ቅዳሜ መጋቢት 28/2016 በብቸና ከተማ ባል እና ሚስት በጥይትና በስለት እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ግድያ የተፈፀመባቸው እና በጎንደር ከተሞች ስላማዊ ምዕመናን መገደላቸውንም ምክር ቤታችን በሐዘን ሰምቷል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ስምንት ወራት፣ በተለይ ሙስሊሞችን ዒላማ በማድረግ ግድያዎች፤ እገታዎች፤ ዘረፋዎች እና የማፈናቀል ተግባራት ሲፈፀሙ መቆየታቸውን ተረድተናል፡፡

በአጠቃላይ መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ምዕመናን የተገደሉ፣ የታገቱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከፍተኛ ዝርፊያዎች ተፈጽመዋል።

የተለያዩ ሃይማኖትና እምነት ተከታዮች ለአያሌ ዘመናት አብረው በሰላም በኖሩባት ሀገራችን፣ ዜጎችን በሃይማኖታቸው ሳቢያ ልዩነት በመፍጠር የጥቃት ዒላማ ማድረግ፣ የሀገርን ሰላም እናየሕዝብን አብሮነት በእጅጉ የሚጎዳ፣ አስከፊ ማኅበራዊ ጠባሳ የሚያስከትል፣ ኃላፊነት የጎደለውና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው::

ሰዎች የተለያየ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል:: ነገር ግን ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ በመግደልና በማሸበር ሊያሳኩ የሚችሉት ምንም ዓይነት ግብ ይኖራል ብለን አናምንም::

ሰላማዊ ዜጎችን በሃይማኖት ለይቶ የማጥቃት እርምጃ፣ በማንም ይፈፀም በማን የሽብር ተግባር እንጂ፣ የትኛውንም ሃይማኖት ወይም ብሔር የሚወክል ተግባር ነው ብለንም አናምንም። በመኾነ-ም፣ በአማራ ክልል በተደጋጋሚ እየተፈፀሙ ያሉትን ሙስሊሞችን ዒላማ ያደረጉ የግድያ፣ የእገታ እና የዘረፋ ጥቃቶች በጽኑ እናወግዛቸዋለን፡፡

ይህ የጥፋት ክብሪት ዉሎ አድሮ ሁላችንንም ሊያነደን የሚችል በመኾኑ፣ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ዛሬውኑ በጥብቅ ሊያወግዙት ይገባል ብለንም እናምናለን።

ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል።

@Esat_tv1
@Esat_tv1