Get Mystery Box with random crypto!

ልጆችን አክብሯቸው፤ ፍርሃት አልባ አ'ርጓቸው... ልጆችን አክብሩ ምክንያቱም እነርሱ ለሕይወት ም | ermi ye hawii.....✍

ልጆችን አክብሯቸው፤ ፍርሃት አልባ አ'ርጓቸው...

ልጆችን አክብሩ ምክንያቱም እነርሱ ለሕይወት ምንጭ ቅርብ ናቸው፤ እናንተ ሩቅ ናችሁ፡፡ እነርሱ ገና ኦርጅናል ናቸው፤ እናንተ አንደኛውን ቅጂ ከሆናችሁ ዘመንም የላችሁ፡፡ እና ደግሞ ልጆችን ማክበር ምን እንደሚፈጥር ታውቃላችሁ ? ፍቅር እና አክብሮታችሁ በተሳሳተ ጎዳና እንዳይነጉዱ ያድናቸዋል - በማስፈራራት ሳይሆን ፍቅር እና አክብሮታችሁ...

አያቴ ማለት ... ማንንም ልዋሽ እችላለሁ - እግዚአብሄርን ባገኘው እንኳ ምንም ሳይመስለኝ ልዋሸው እችላለሁ - አያቴን ግን፣ እጅጉን ስለሚያከብረኝ ፈጽሞ ልዋሸው አልችልም ! መላው ቤተሰብ እኔ ላይ ሲነሳ፣ መመኪያዬ ያ ሽማግሌ ነበር፡፡ እኔ ላይ የሚቀርበው ስሞታ እና የማስረጃ ናዳ ጉዳዩ አይደለም፡፡ “የፈለገውን ያድርግ፡፡ ካደረገው ትክክል ነው ማለት ነው፡፡ አውቀዋለሁ፤ ስህተት አይሰራም” ይልልኛል፡፡

እናም እርሱ እኔን ደግፎ ከጎኔ ሲቆም መላው ቤተሰብ ኩምሽሽ ይላል፡፡ እኔም ያደረግኩትን ሁሉ እነግረዋለሁ፡፡ እርሱም እንዲህ ይለኛል፣ “ምንም አታስብ፡፡ ተገቢ ነው የምትለውን ሁሉ አድርግ፡፡ እና ታዲያ አንተ ማድረግ ያለብህን ማን ሊወስንልህ ነው ? አንተ ባለህበት ሁኔታ፣ ባንተ ቦታ ... ካንተ ውጪ ማንም መወሰን አይችልም ... አንተ ነህ መወሰን ያለብህ፡፡ ትክክል ነው ብለህ የሚሰማህን ሁሉ አድርግ፤ እናም ሁሌም ከጎንህ መሆኔን አስታወስ፡፡ ምክንያቱም እኔ አንተን መውደድ ብቻ አይደለም አከብርሃለሁም...”

በሕይወቴ የታደልኩት ትልቁ ሐብቴ እርሱ ለእኔ ያለው አክብሮት ነበር፡፡ ሊሞት ሲል እኔ 80 ማይል በራቀ ቦታ ነበርኩ፡፡ ጊዜ የለኝም ቶሎ ድረስ ብሎ ላከብኝ፡፡ በሁለት ሰዓት ውስጥ ደረስኩ፡፡

ሞቱን አዘግይቶ እኔን እየጠበቀኝ ያለ ነበር የሚመስለው፤ እናም ዓይኖቹን ገልጦ እንዲህ አለኝ፣ “አንተ እስክትመጣ ነበር እንደምንም ትንፋሼን ያቆየሁት፡፡ አንድ ነገር ብቻ ልልህ እፈልጋለሁ - ከአሁን በኋላ ከጎንህ ቆሜ ልደግፍህ አልችልም - ግን ድጋፍ ያሻሃል፡፡ እናም አስታውስ ... የትም ልሁን የት፣ ፍቅሬ እና አክብሮቴ መቼም ቢሆን ካንተ ጋር ነው፡፡ ማንንም አትፍራ፤ ዓለምን ጨርሶ አትፍራ...”

አዎን የመጨረሻ ቃላቱ እኒህ ነበሩ፣ “ዓለምን ጨርሶ አትፍራ”
ልጆችን አክብሯቸው፤ ፍርሃት አልባ አድርጓቸው፡፡
ግን እናንተ ራሳችሁ በፍርሃት የተሞላችሁ ሆናችሁ ሳለ እንዴት ሆኖ ነው እነርሱን ፍርሃት አልባ ልታደርጓቸው የምትችሉት ?

ገና ለገና አባት፣ እናት ምናምን ስለሆናችሁ ብቻ አክብሩኝ አትበሉ፡፡

ይህን አመለካከት ለውጡትና አክብሮት ልጆቻችሁ ላይ የሚያመጣውን ለውጥ እዩ፡፡

ልጆች ... የምታከብሯቸው ከሆነ በጣም በጥንቃቄ ይሰሟችኋል፡፡ የምታከብሯቸው ከሆነ እናንተን እና አእምሯችሁን በጣም በጥንቃቄ ለመረዳት ይጥራሉ፡፡ መሆንም አለበት፡፡ እናም በምንም መንገድ የትኛውንም ነገር አትጫኑባቸው፡፡ በራሳቸው መረዳት የእናንተ መንገድ ትክክል እንደሆነ ተሰምቷቸው በዚያ መንገድ ከሄዱ፣ እውነተኛውን የነፍሳቸውን መልክ አያጡትም !

እውነተኛው እና ኦርጅናሉ የነፍስያ መልክ በሆነ መንገድ ስለተጓዙ አይጠፋም፡፡ ይልቁንም፣ ልጆች ያለፍቃዳቸው በግዳጅ ባልፈቀዱት መንገድ እንዲሄዱ ሲደረጉ ነው ኦርጅናሉን የነፍሳቸውን መልኩ የሚያጡት...

ፍቅር እና አክብሮት፣ ልጆች፣ በተዋበ መልኩ ስለዓለም የላቀ መረዳት እንዲኖራቸው፣ ይበልጡን ንቁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል - ምክንያቱም ሕይወት ውድ የሁለንተና ስጦታ ነች - ልናባክናት አይገባም፡፡

ምንጭ - Osho, From Darkness to Light, Ch 6, Q 1 (excerpt)