Get Mystery Box with random crypto!

ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ችግሮችን ማስወገድ ተማር!! ጥበብ ሕይወትን የምንቀዝፍባቸው ክህሎቶች መ | ermi ye hawii.....✍

ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ችግሮችን ማስወገድ ተማር!!

ጥበብ ሕይወትን የምንቀዝፍባቸው ክህሎቶች መለኪያ ነው። ችግሮችን አስቀድሞ መከላከል ከተፈጠሩ በኋላ ከመፍታት የተሻለ ጥበብን ይጠይቃል፡፡እውነታው ሕይወት ከባድ መሆኗ ነው፡፡ ችግሮች በሁሉም አቅጣጫ በየጊዜው ይተኮሱብሃል፡፡ እጣ ፈንታ መርገጫህ ስር ጉድጓዶችን ልትቆፍርብህ ወይም መሿለኪያዎችህን ልትዘጋብህ ትችላለች። ይህንን መቀየር አትችልም፡፡ አስቀድሞ አደጋ ያለው የት ጋር እንደሆነ ከተረዳህ ግን ወዳንተ እንዳይመጣ ለማጠር እድል ይኖርሃል፡፡ በዚህ መንገድ መሰናክሎችን ሁሉ ማስወገድ ትችላለህ፡፡ ይህንን ሀሳብ አልበርት አንስታይን እንዲህ ያስቀምጠዋል፡፡ “ጎበዝ ሰው ችግሮችን ይፈታል፤ ጥበበኛ ሰው ግን ችግሮችን ያስወግዳል፡፡”

ችግሩ ችግሮችን ማስወገድም የሚወደስ ነገር አለመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ፊልሞችን አስብ፡፡
1.በመጀመሪያው ፊልም ውስጥ አንድ መርከብ ከበረዶ ክምር ጋር መጠነኛ ግጭት ይገጥመዋል፡፡ መርከቡም ይሰምጣል። በዚህ ጊዜ የመርከቧ ካፒቴን ራስ ወዳድነት በሌለበት መልኩ ራሱን አበርትቶ ተሳፋሪዎቹን ሁሉ ከመስመጥ ይታደጋቸዋል፡፡ መርከቧ ለዘለዓለሙ ከመሰወሯ ከደቂቃዎች በፊት ሁሉንም ተጓዦች በማዳን ከጀልባው ላይ ዘሎ ወደ ሕይወት አድኑ ቦቴ ውስጥ በመግባት የመጨረሻው ሰው ነበር።

2.በሁለተኛው ፊልም ውስጥ ደግሞ እንዲህ ሆነ፡፡ መርከበኛው መርከቧ ከበረዶ ክምሩ ጋር ከመጋጨቷ በፊት አስተውሎ በቂ ርቀት ላይ እንድትቆም አደረጋት፡፡

የትኛውን ፊልም ለማየት የበለጠ ትከፍላለህ?በእርግጠኝነት የመጀመሪያውን ፊልም፡፡ ሌላ ጥያቄ ደግሞ ላንሳልህ፡፡ አንተ በመርከቧ ውስጥ ተጓዥ ብትሆን ኖሮ በየትኛው ፊልም ሁኔታ ውስጥ መሆንን ትመርጣለህ? ያለ ምንም ጥርጥር ሁለተኛው ፊልምን።

እነዚህ ምሳሌዎች እውነተኛ ገጠመኞች ናቸው ብለን እናስብ፡፡ ቀጥሎ ምን ይፈጠራል? የመጀመሪያው ፊልም ውስጥ ያለው ካፒቴን የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ይጋበዛል። ምናልባት መርከበኛነቱን ትቶ አነቃቂ ንግግሮችን እያደረገ ሕይወቱን መምራት ሊጀምር ይችላል። መንገድም በስሙ ሊሰየምለት ይችላል፡፡ ልጆቹም (ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ) በአባታቸው ይኮራሉ፡፡ የሁለተኛው ፊልም ውስጥ የሳልነው ካፒቴንስ? ከስራው በጡረታ እስኪገለል ድረስ ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅድመ ጥንቃቄ የመርከበኝነት ስራውን ይሰራል። መርሁም “ከ20 ጫማ እርቀት ላይ ልታልፈው የምትፈራውን ነገር በ500 ጫማ እርቀህ እለፈው” የሚለው የቻርሊ ሙገር የሕይወት መርህ ይሆናል፡፡

እንግዲህ ተመልከት፡- የሁለተኛው ፊልም ካፒቴን ከመጀመሪያው ፊልም ካፒቴን በሚታይ መልኩ የሚሻል ቢሆንም እኛ የምናከብረውና የምናደንቀው ግን የመጀመሪያውን ፊልም ካፒቴን ነው፡፡ ለምን? በቅድመ ጥንቃቄ የሚመጣ ስኬት ለውጪው ዓለም እይታ የሚጋለጥ አይሆንም፡፡

ጋዜጠኞች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳይመጡ ካረጉ በሳል ሰዎች ይልቅ ችገሮችን የቀለበሱ የሥራ መሪዎችን ነው የሚያሞካሹት ።የቅድመ ጥንቃቄ ስኬቶች ለውጪው ዓለም የማይታዩ ባለመሆናቸው ምክንያት ሳይታዩና ሳይወደሱ ይኖራሉ፡፡ የእንደዚህ አይነት ስኬቶት ባለቤቶችን ጥበብ የሚያውቁት በእሱ ዙሪያ ያሉ የቡድኑ አባላት ብቻ ናቸው። እነሱም ቢሆን በተወሰኑ መልኩ ቢያውቁት ነው፡፡

የአንተስ ሕይወት? አመንክም አላመንክም ከስኬቶችህ ሁሉ 50% የሚሆኑት የቅድመ መከላከል ጥንቃቄህ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሁላችንም እንደምናደርገው ሁሉ አንተም አንዳንድ ነገሮችን በንዝህላልነት ልታደርግ ትችላለህ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖም ግን ስህተቶችን ላለመስራት ሁልጊዜም ትጠነቀቃለህ፡፡ በአርቆ · አሳቢነት ያስወገድካቸውን በስራህ፣ በትዳርህ፣ በትምህርትህ ወይም በሌላ የሕይወትህ ዘርፍ ሊገጥሙህ የነበሩ ችግሮችን አስብ፡፡

ጥንቃቄ (prevention) ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ቅድመ ጥንቃቄ በባህሪው ቀድሞ ማየት (imagination) ይጠይቃል ቀድሞ መረዳትና የሚመጣውን መገመት ደግሞ ብዙውን ጊዜ አዛብተን የምንረዳቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ አዲስ ሀሳብ አያመጣልንም፡፡ በዓይነ ህሊና ማየት (imagination) ማለት የመጨረሻው ፍትሃዊ ነገር ሆኖ እስክናይ ድረስ ሊሆኑ የሚችሉት ነገሮች ውጤቶችና የመፈጠር እድላቸውን ሁሉ እንዲያስብ አዕምሯችንን ማሰራት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም አስቀድሞ ማየትና መገመት ከባድ ስራ ነው።

በተለይ ጉዳዩ ስለአደገኛ ችግሮች ሲሆን ደግሞ ቀድሞ የመገመት ሥራ የበለጠ ፈታኝ ይሆናል፡፡ ሊመጡ እድል ባላቸው ችግሮች ላይ ሁሉ እየተጠነቀቅክ መኖር ይጠበቅብሃል? ይህስ ሁልጊዜ የተጨናነቀ ሰው ሆነህ እንድትኖር አያደርግህም? ተሞክሮዎች የሚያሳዩት እንደዚያ እንዳልሆነ ነው፡፡ ቻርሊ ሙገር እንዲህ ይላል “በሕይወት ዘመኔ ሁሉ የሚመጠብኝን አደጋዎች ስገምት ኖሬያለሁ፡፡ ሁልጊዜ ይሄንን እያሰብኩ፣ አደጋዎች ከመጡም እንዴት መመከት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ መኖሬ ደስተኛ እንዳልሆን አላደረገኝም፡፡”