Get Mystery Box with random crypto!

እምቢ የማለት ጥበብ በዓለማችን ላይ ብዙ ሰዎችን ከሚያጠቁ አጉል ጠባዮች አንዱ ‘አይሆንም’ ማለ | ermi ye hawii.....✍

እምቢ የማለት ጥበብ

በዓለማችን ላይ ብዙ ሰዎችን ከሚያጠቁ አጉል ጠባዮች አንዱ ‘አይሆንም’ ማለት ያለመቻል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በፍጹም ማድረግ የማይፈልጉትን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከቤተሰብ፣ ከዘመድ ወይንም ከጓደኛ በሚኖር ጫና ብቻ ‘አይሆንም’ ወይም ‘አልፈልግም’ ማለት ሳይችሉ ቀርተው እና የማይፈልጉትን ትምህርት መርጠው ሙሉ ሕይወታቸውን በማይሆን አቅጣጫ የቀየሱ ሰዎችን በግሌ አውቃለሁ፡፡ ይህ ‘እምቢ’ ማለት አለመቻል እጅግ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ የሥነ-ልቡና ምሁራን ‘ከሌሎች ውጫዊ ተጽእኖ መላቀቅ መቻል አንድ ሰው በሕይወቱ ከሚያስመዘግባቸው ድሎች እጅግ የላቀው ነው’ እስከማለት ደርሰዋል፡፡

አንድ ሰው ከእንቅልፉ ሲነሳ ብዙ ነገሮች ጊዜውን እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ስልኩ ይጮሃል፣ በኢሜይል መልእክት ይመጣለታል፣ የቅርብ ጓደኛው ቀጠሮ ለማስያዝ ይሞክራል፣ አለቃው ተጨማሪ ሥራ ሊያዘው ያስጠራዋል… ወዘተ፡፡ በዚህ መልኩ የዚያን ሰው ጊዜ ለሚፈልጉ ነገሮች በአጠቃላይ ‘እሺ’ የሚል ከሆነ መሥራት ያለበትን ሥራ በተገቢው ፍጥነት እና ጥራት መሥራት አይችልም፡፡ ሁሉንም እሺ በማለቱ እጅግ ይጨናነቃል፡፡ አንድ ሰው የራሱን ሥራ ጨርሶ ሌላ ፕሮግራም እያለው፤ ሥራውን ሳይሠራ የቀረ ባልደረባው ‘ይህቺን ሥራልኝ’ ቢለው እና ‘ይቅርታ፣ ዛሬ ሌላ ፕሮግራም አለኝ…’ ማለትን ሳይችል ቀርቶ ‘እሺ’ ቢለው፤ ፕሮግራሙን ማበላሸቱ አይደለም? በዚህ ምክንያት የሚበላሹ ነገሮችን ለማዳን እና ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ካስፈለገ በተገቢው መንገድ ‘አይሆንም’ የማለት ጥበብን መልመድ የግድ ይላል፡፡

ሰዎች ‘አይሆንም’ ማለት የማይችሉባቸውን ምክንያቶች የሚዘረዝሩ የሥነ-ልቡና ምሁራን ሁለት ዋና ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ሌላኛውን ሰው ለማስቀየም አለመፈለግ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ይህ ሰው እጅግ የምንወደው፣ የምናከብረው ወይም ደግሞ የቅርብ ሰው ከሆነ ‘እንዳላስቀይመው’ ወይንም ‘እንዳላስቀይማት’ በሚል ሰበብ ሁሉንም ነገር እሺ ማለት ያለብን ይመስለናል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከዚያ ሰው ጋር ዘላቂ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ፤ ‘አይሆንም’ ማለታችን ግንኙነታችንን ክፉኛ እንዳይጎዳው ከማሰብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክፉ ሆኖ መታየትን በመፍራት፣ ከቡድን መገለልን በመፍራት፣ ግጭትን በመፍራት እና እድል ያመልጠኛል በሚል ፍራቻ ሰዎች ‘አይሆንም’ ማለት ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ በአስተዳደጋቸው ወቅት ‘አንተ! እሺ በል እንጂ!’ ወይም ‘አንቺ! እሺ አትይም?’ እየተባሉ ያደጉ ልጆች፤ እንዲህ አይነት ‘እሺ ባይነት’ ጠባይ ሊያጠቃቸው እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ያብራራሉ፡፡

በመሆኑም፤ በተገቢው መልኩ ‘አይሆንም’ የማለት ጥበብን ማዳበር ጊዜያችንን በፈለግነው መልኩ እንድንጠቀም ከማስቻሉም በተጨማሪ ከአላስፈላጊ ተጽእኖ እና ከሚፈጠር ጭንቀት ሊያድነን ይችላል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ ዶ/ር ኢዮብ ማሞ ‘የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ’ በሚለው ላይ ‘ትሁት አምቢታ’ እንዴት ሊጠቅመን እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ ፊት ለፊት ‘እምቢ’ ማለት የእውነትም ሰዎችን የሚያስቀይም ሊሆን ቢችልም፤ የትሁት እምቢታ ጥበብን ከለመድን ግን በቀላሉ ማስተናገድ እንችላለን፡፡ ምስሉን አብሬ አያይዣለሁ፤ በፓውሎ ኮኤልሆ ጥቅስ ጽሑፉን ልጠቅልል፡፡

‘ለሌሎች ‘እሺ’ ስትል ራስህን ግን ‘እምቢ’ እያልክ አለመሆኑን አረጋግጥ’ ፓውሎ ኮኤልሆ

@ermiyee1
@ermiyee1