Get Mystery Box with random crypto!

የልጆች ማህበራዊ እና ሀይለ-ስሜታዊ እድገት(social and emotional development) | ermi ye hawii.....✍

የልጆች ማህበራዊ እና ሀይለ-ስሜታዊ እድገት(social and emotional development)


   ማህበራዊ እድገት ለሰው ልጅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የእድገቶች አይነት ውስጥ አንዱ  ነው፡፡ማህበራዊ እድገት የሚጀምረው ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ልጆች ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ የምናደርግላቸው ነገሮች የልጆች ማህበራዊ እድገት ላይ የራሳቸው የሆነ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽእኖ አላቸው፡፡በዚህ መስክ ብዙ የተመራመረው ተመራማሪ ኤሪክ ኤሪክሰን ሰዎች ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ እስከ እርጅና ድረስ ያለውን  የሰዎች የማህበራዊ እድገትን በስምንት ደረጃዎች ይከፍላቸዋል፡፡እነዚህ ስምንት ክፍሎች በእድሜ ክልል የተከፋፈሉ ሲሆን በአንደኛው ደረጃ ላይ ያለው የማህበራዊ እድገት ለቀጣዩ መሰረት ነው፡፡ ስምንቱን ደረጃዎች ከዚህ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡

1.ማመን ወይም አለማመን( Trust Versus Mistrust)

   ይህ የእድገት ደረጃ ልጆች ከተወለዱ ጀምሮ እስከ አንድ አመት ተኩል ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡በዚህ እድሜ ላይ ያሉ ልጆች ፍላጎታቸውን የሚገልጹት በማልቀስ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በሚደረግላቸው እንክብካቤ መጠን እና ቀጣይነት ሌሎችን ማመን ይጀምራሉ፡፡በዚህ ወቅት ላይ በአግባቡ የሚፈልጉት ነገር ከተሟላላቸው አለምን ማመን ይጀምራሉ የደህንነት ስሜትም ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን የሚፈልጉትን ነገር በአግባቡ እና ወጥ በሆነ መልኩ የማናሟላላቸው ከሆነ መጠራጠር እና መፍራት ይጀምራሉ፡፡በዚህም የተነሳ መጨነቅ፣ፍርሀት እና ከፍተኛ የሆነ እምነት ማጣት ሊታይባቸው ይችላል፡፡

2. በራስ መተማመን ወይም ማፈር እና እራስን መጠራጠር( Autonomy vs. Shame and Doubt)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ አንድ አመት ተኩል እስከ ሶስት አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡በዚህ ጊዜ ውስጥ ልጆች መንቀሳቀስ የሚጀምሩ ሲሆን እቃ ማንሳት በአሻንጉሊት መጫወት ይፈልጋሉ፡፡ ምግብም እራሳቸው መመገብ ፣ልብሳቸውን እራሳቸው መልበስ….ወዘተ ይፈልጋሉ፡፡ እራሳችን እንስራ በሚሉበት ጊዜ እንዲሰሩ  የምናበረታታቸው ከሆነ በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ያዳብራሉ፡፡እራሳቸውን ችለው በዚህ አለም ላይ የመኖር ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የምንተቻቸው ከሆነ  እንዳይሰሩ የምንቆጣጠራቸው ከሆነ ወይም ሁሉንም ነገር እኛ የምንሰራላቸው ከሆነ ነገሮችን ለመሞከር ሲያፍሩ ወይም እራሳቸውን ሲጠራጠሩ ይታያሉ፡፡

3. መነሳሳት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት( Initiative vs. Guilt)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ ሶስት አመት እስከ ስድስት አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ልጆች በዚህ እድሜ መጫወት ይጀምራሉ፣ለሚሰሩት ስራ እቅድ ያወጣሉ፣ለጫወታ ይነሳሳሉ ሌሎችንም ያነሳሳሉ …ወዘተ ልጆች ይሄ እድል ከተፈጠረላቸው የተነሳሽነት ስሜት እና በራሳቸው ችሎታ የመተማመን ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ነገር ግን እገዳ የምንጥልባቸው ከሆነ ወይም የምንቀጣቸው ከሆነ የጥፋተኛነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ነገሮችን በራሳቸው ለመስራት ከመነሳሳት  ይልቅ ሌሎችን መከተል ይመርጣሉ፡፡

4. በሰሩት ስራ መኩራት ወይም የበታችነት ስሜት መሰማት( Industry vs. Inferiority)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ ስድስት አመት እስከ አስራአንድ አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች መደበኛ ትምህርት ይጀምራሉ፡፡ልጆች በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ በሰሩት ስራ የመኩራት ባህሪን ያሳድጋሉ፡፡ስራን ጀምረው ሲጨርሱ የኩራት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡አስተማሪዎች ልጆችን በማነሳሳት እና ያሰቡትን ግብ እንዲያሳኩ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጾ አላቸው፡፡ በዚህም ልጆች ስራን እንዲሰሩ ከተበረታቱ እና በሰሩት ስራ ሽልማት ከተበረከተላቸው በራሳቸው ስራ የመኩራትን ባህሪ ያሳድጋሉ ከዚህም በተጨማሪ ያሰቡትን ግብ እንደሚያሳኩ በራሳቸው ላይ እምነት ይኖራቸዋል፡፡ነገር ግን በወላጅ ወይም በአስተማሪ ገደብ የሚጣልባቸው ከሆነ ወይም የሚቀጡ ከሆነ እራሳቸውን ይጠራጠራሉ፣የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል እንዲሁም የአቅማቸው ጫፍ ላይ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡

5.ማንነትን መለየት ወይም ግራ መጋባት( Identity vs. Role Confusion)

   ይህ የእድገት ደረጃ ከ 11 አመት እስከ አስራስምንት አመት ባለው ጊዜ ውሥጥ ያለ የእድገት ደረጃ ነው፡፡ይህ ወቅት የጉርምስና ወቅት ነው፡፡ጉርምስና ልጆች ከህጻንነት ወደትልቅነት የሚተላለፉበት ድልድይ ነው ልጆች በዚህ ወቅት ላይ እራስን ችሎ መንቀሳቀስ፣ ወደፊት ምን መሆን እንደሚፈለጉ መወሰን ፣ጓደኞቻቸውን መምረጥ …ወዘተ ይፈልጋሉ፡፡ልጆች በዚህ ጊዜ ላይ በዙሪያቸው ያሉ አማራጮችን ከማየታቸውም በተጨማሪ እራሳቸውን መፈለግ ይጀምራሉ በዚህም የተነሳ እኔ ማነኝ የሚለውን ጥያቄ ይመልሳሉ አካባቢያቸው ይህን ካልፈቀደላቸው ግን ግራ መጋባት ይፈጠርባቸዋል ወደፊት ምን መሆን እንደሚፈልጉም አያውቁም፡፡