Get Mystery Box with random crypto!

የይመስለኛል ፖለቲካ አንዳንድ የብሄር ፖለቲከኞች ደጋፊዎቻቸውን ለማሳመን የሚጠቀሟቸው ቃላቶች ያስ | Yihune Ephrem Kassahun

የይመስለኛል ፖለቲካ

አንዳንድ የብሄር ፖለቲከኞች ደጋፊዎቻቸውን ለማሳመን የሚጠቀሟቸው ቃላቶች ያስቁኛል። ከእነዚህም መካከል አንደኛው የተወሰኑ ብሄሮች በማንነታቸው በስማቸው ጭምር እንዲሸማቀቁ ይደረግ ነበረ የሚለው ትልቁ ማሳመኛቸው ነው ሆኖም ይህ ደጋፊን ለማፍራት ሆን ተብሎ የተቀመረ ማሳመኛ ነው፤ ሰው በስም መጠሪያው እንዲሸማቀቅ ይደረግ የነበረው አሁንም የሚደረገው በአንድ ብሄር ላይ ብቻ ሣይሆን በኦሮሞውም፣ በደቡቡም በአማራውም ላይ ጭምር ነው። ጥሩ ምሳሌ ልንገራችሁ ድምፃዊ ኤልያስ ተባባል የተወለደው ጎንደር ነው አዲስ አበባ መጥቶ የሙዚቃ ካሴት ሊያሳትም አሳታሚዎችን ሲጠይቅ ትክክለኛ ስሙን ልዋጥህ ተባባልን ካልቀየረ ህዝቡ ካሴቱን እንደማይገዛው ተነግሮት ነው ከልዋጥህ ተባባል ወደኤልያስ ተባባል የቀየረው የማዲንጎ አፈወርቅም ስም ተቀይሮ እንደሆነ ሰምቻለሁ እርግጠኛ ባልሆንም ትክክለኛ ስሙ ተገኝ ነው የሚል ነገር ሰምቻለሁ፤ ተገኝ የሚለው ስም አሸማቆት ነው ማዲንጎ ያስባለው። በርካታ የአማራ ተወላጅ አዲስ አበባ ሲገባ ከድላርጋቸው ወደዳጊ ከእማዋይሽ ወደኤሚ ከፈለቀ ወደፊሊሞን ስሙን ይቀይራል። ይህንን የሚያደርጉት በስማቸው ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የሚያጋጥማቸውን ተረብ በመፍራት ነው። በኦሮሞውም ላይ የሆነው ተመሳሳይ ነው በርካታ ኦሮሞዎች አዲስ አበባ ሲመጡ ስማቸውን ይቀይራሉ።

በነገራችን ላይ ሰውን በስም ማሸማቀቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሀገር ያለ ነው ለምሳሌ የጀርመንን ብንመለከት Schartzmugel የሚለው ስም መጠሪያቸው የሆኑ ሴቶች በብዛት በስማቸው ይቀልድባቸዋል የእነርሱ ስም ዘመናዊ እንዳልሆነና እንዲቀይሩት ሲነገራቸው ልትሰሙ ትችላላችሁ በአንፃሩ Katrina በጣም ተወዳጅ የጀርመን ሴቶች ስም ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው በስሙ እንዲያፍር የሚደረገው ጎሣ እየተመረጠ አይደለም ከሁሉም ጎሳዎች ስም እየተመረጡ አዲስ አበባ ላይ ሰው ለመቀለድ ይሞክራል። ደሚቱ የሚለው የኦሮምኛ ስም ሲተረጐም ማሪቱ እንደማለት ነው ሆኖም በዚህ ሰአት ልጅህን ማሪቱም አልካት ደሚቱ ስሟን ሰምቶ የሚስቅ ሰው አታጣም ይህ የሰው ልጅ ለስም ካለው ግምት የሚነሳ ነው እንጂ አንዱን ጎሣ በመናቅ ሌላውን ለማሞገስ ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም አልነበረምም።

ኢትዮጵያውያን ከሚለያዪን ነገሮች ይልቅ የምንመሳሰልባቸው ነገሮች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ ሊለያዩን የሚሯሯጡትን እያስወገደን አንድነታችንን ማጠናከሩ ለሁላችንም መልካም ነው።