Get Mystery Box with random crypto!

#የምንለወጠው_ምን_ስናደርግ_ነው? በታመምህ ጊዜ ድካም ይሰማሃል፤ ብርታት ያንስሃል፤ ፊትህም ይገ | ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች

#የምንለወጠው_ምን_ስናደርግ_ነው?

በታመምህ ጊዜ ድካም ይሰማሃል፤ ብርታት ያንስሃል፤ ፊትህም ይገረጣል፡፡ የዕለት ተዕለት ሥራዎችህን በአግባቡ ማከናወን ይሳንሃል፡፡ በዚህ ጊዜም ሕመምህ ምን ያህል እንደ በረታ ሰዎች ያስተውላሉ፤ መታከም እንደሚገባህም ይነግሩሃል፡፡ ስለዚህ ወደ ሐኪም ትኼዳለህ፡፡ ወደ ሐኪም የምትኼደው ግን ሐኪሙ ምን እንዲያደርግልህ ነው? አሁን ለሚሰሙህ ስሜቶች የሚሽሩ መድኃኒቶችን እንዲሰጥህ ነው፡፡ ኾኖም ይሰ'ሙህ የነበሩ ስሜቶች ቢሻሉህም ሰውነትህ አሁንም እንደ ደከመ፣ ፊትህ እንደ ገረጣ ከቀረ፣ የዕለት ተዕለት ሥራዎችህንም በአግባቡ ማከናወን ከተሳነህ በተሰጠህ ሕክምና ደስተኛ ትኾናለህን? አትኾንም !

“እውነታው ምንድን ነው?” ስንል ወደ ሐኪሙ የኼድከው የበሽታህን ምንጭ ለመታከም ሳይኾን የበሽታህን ምልክቶች ለማስታገሥ ስለኾነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የበሽታህ መንሥኤ እስካልታከመ ድረስ የበሽታህ ምልክቶች ለጊዜው ቢታገሡም ቅሉ ፈጽመው ሊወገዱ እንደ ማይችሉ ሐኪሙ በደንብ ያውቃል፡፡

በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉድ፣ በመንፈስ ቅዱስም መንፈሳውያን የተባልን እኛም እግዚአብሔር መንፈሳዊ በሽታችንን እንዲያስወግድልን እንሻለን፡፡ እንደ እውነታው ግን ብዙዎቻችን ወደ እግዚአብሔር ቀርበን እንዲያስወግድልን የምንሻው ምልክቶቹን ነው፡፡ ለምሳሌ ችግርን፣ ኀዘንን፣ ቀቢጸ ተስፋንና የመሳሰሉትን እንዲያርቅልን እንፈልጋለን፡፡

እግዚአብሔር ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የእነዚህ ምክንያት የኾነውንና ሥር የሰደደውን፣ ዋና ምክንያትም የኾነውን መንፈሳዊ በሽታችንን ሳይሽር እነዚህን ምልክቶች ሊያርቅልን አይፈልግም፡፡ ችግር የሚኾነውም ይህን ጊዜ ነው፡፡ ምልክቶቹን እንዲያርቅልን ስንደክም ወደ ውሳጤያችን ገብቶ የችግሩን ምንጭ ሊያርቅልን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ (ኃይልን) አጥብቀን እንቃወማለንና፡፡ በውሳጤያችን የተሸሸገውን በሽታ ማስወገድ አንፈልግም፡፡ አመለካከታችን እንዲለወጥ አንፈቅድም፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣውና አማን በአማን የምንታከመው ግን የልባችንን ውሳጤ ለእግዚአብሔር ስንከፍትለትና እርሱም በዚያ በመረቀዘው ቁስላችን ላይ ጽኑ መድኃኒት ሲያስርልን ነው፡፡ እንዲለወጡ የምንፈልጋቸው ምልክቶች በእርግጥም የሚለወጡት ይህ በልባችን ውስጥ የተደበቀው መንፈሳዊ በሽታችን ሲጠፋ ነው፡፡

➛ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
➛ አምስቱ የንስሐ መንገዶች - ገጽ 69-70
➛ ትርጉም በገብረ እግዚአብሔር ኪደ

@eotcy