2022-07-30 05:32:43
† እንኳን ለእናታችን ቅድስት መሪና ሰማዕት እና ቅዱስ ለንጊኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። †
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
† ታላቋ ቅድስት መሪና ሰማዕት [SAINT MARINA THE GREAT] †
† እናታችን ቅድስት መሪና ስም አጠራራቸው ከከበረ : ተጋድሏቸው ካማረ ታላላቅ ሴት ሰማዕታት አንዷ ናት:: ተወልዳ ያደገችው ከዋናው ዘመነ ሰማዕታት በፊት በ፪ [2] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሶርያ አካባቢ ነው:: አባቷ ዳኬዎስ የሚባል ጣዖት አምላኪ ቢሆንም እናቷ ግን ክርስቲያን ነበረች::
ነገር ግን እናቷ ገና በ፭ [5] ዓመቷ ሞተችባትና ለሞግዚት ተሰጠች:: የእግዚአብሔር ጥበብ ሆኖ ሞግዚቷ ደግ ክርስቲያን ነበረችና ለ፲ [10] ዓመታት ሃይማኖተ ክርስቶስን እና ምግባረ ጽድቅን አስተማረቻት:: ዕድሜዋ ፲፭ [15] ዓመት ሲሆን አባቷ ዳኬዎስ አረፈ::
በዘመኑ ዳኬዎስ የሚሉት [ቅዱስ መርቆሬዎስን የገደለው] ክፉ ንጉሥ ነበርና ክርስቲያኖችን አሳደዳቸው:: ይህን ዜና ቅድስት መሪና ስትሰማ ደስ አላት:: እጅግ ባማረ ንጽሕና እንደ ኖረች ሁሉ በክርስቶስ ስም ደሟን ለማፍሰስ አስባ ወደ ንጉሡ መኮንን ሔደች::
† አበው እንዳስተማሩን ከሴቶች ሰማዕታት በውበትና ደም ግባት እንደ ቅዱሳት :-
- መሪና
- አርሴማ እና
- ጣጡስ የሚያክል የለም:: ዐይንን ማፍዘዝ የሚችል ውበት ነበራቸው::
መኮንኑ መልኩዋን ዐይቶ ሰውነቱ ተናወጠ:: "ጣዖት አምልኪና የእኔ ሚስት ሁኚ" አላት:: እርሷ ግን መኮንኑን ከነ ጣዖቱ አቃለለችው:: "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ" አለችው::
መኮንኑ ካነጋገሯ የተነሳ ተቆጥቶ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ:: መሬት ላይ ጥለው በብረት ዘንግ ቢመቷት አካሏ እየተቆረጠ ብዙ ደም ፈሰሰ:: ወስደውም ጨለማ ውስጥ ጣሏት:: ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አድኗት: አጽንቷትም ዐረገ::
በማግስቱ በመጋዝ አካሏን ቆራርጠው ጣሉ:: ዳግመኛ ሊቀ መላእክት አዳናት:: ወደ ጨለማ ክፍል ወስደው ሲጥሏት ትልቅ ዘንዶ መጣባት:: እጆቿ ተዘርግተው እጸለየች ዋጣት:: እርሷ ግን ጸሎቷን ቀጠለች:: ከደቂቃዎች በሁዋላ ግን ዘንዶው ለ፪ [2] ተሰነጠቀና እጆቿ እንደተዘረጉ ወጣች::
በሌላ ቀን ግን ሰይጣን ፊት ለፊት መጥቶ ታገላት:: ከሰማይ ነጭ ርግብና መስቀል ወርዶላታልና አልቻላትም:: ከእግሯ በታች ጥላ ደጋግማ ረገጠችው:: ሰይጣንም በሐፍረት እየጮኸ ሔደ::
"ለሰይጣን ኬደቶ ከመ አሣዕን በእግር" እንዲል:: [እንዲህ ነበሩ የቀደመው ዘመን እናቶቻችን]
መኮንኑ ከክርስትና ያስወጣት ዘንድ በትልቅ ጋን ውሃ አስፈልቶ "በዚያ ላይ ቀቅሏት" አለ:: ድንገት ግን ከሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ: ውሃውን አቀዝቅዛ : ፫ [3] ጊዜ በውሃው አጠመቀቻት:: [እስከዚህ ሰዓት ድረስ አልጠመቀችም ነበርና]
ርግቧ የብርሃን ልብስ አልብሳ: አክሊለ ክብር ደፋችላት:: መኮንኑ ተስፋ ስለ ቆረጠ "አንገቷን በሰይፍ ምቱ" አለ:: በዚያች ሰዓት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ "ብጽዕት መሪና ብጽዐን ይገባሻል" አላት::
"ስምሽ በሚጠራበት: መታሰቢያሽ በሚደረግበት ሁሉ በዚያ ረድኤት: በረከት ይበዛል:: አንቺን ያከበረውን አከብረዋለሁ:: ከርስትሺም አስገባዋለሁ" ብሏት ጌታችን ዐረገ::
ወታደሮቹ አንገቷን በሰየፉ ጊዜ ታላቅ መነዋወጽ ሆነ:: ድውያን ተፈወሱ: ዕውሮች አዩ: አንካሶች ረቱ: የማይሰሙትም ሰሙ:: ቅዱሳን መላእክትም ከሰማያት ወርደው የቅድስት መሪናን ነፍስ በዝማሬ አሳረጉ::
† ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት †
† ለንጊኖስ ማለት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ዘመን የዺላጦስ ወታደር የነበረ ሰው ነው:: ስለ ጌታችን ተአምራት በየጊዜው ይሰማ ነበር:: ሔዶ እንዳያገኘው ግን አይሁድን ይፈራ ነበር:: እነርሱ "በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ከምኩራብ ይባረር" ብለው ነበርና:: [ዮሐ.፱፥፳፪] (9:22)
ጌታችን በተሰቀለባት ዕለተ ዐርብ ግን ጭንቅ ሆነበት:: ጌታን እንዲሰቅሉ ከታዘዙ ወታደሮች እንደ አንዱ ተመርጦ ነበርና በዘዴ "አሞኛል" ብሎ እስከ ፱ [9] ሰዓት ድረስ ቆየ::
በሁዋላ ግን አይሁድ "በክርስቶስ ሞት ያልተባበረ ሁሉ ወንጀለኛ ነው" የሚል አዋጅ በማስነገራቸው እየፈራ ቀራንዮ ሲደርስ "ጐኑን ውጋው" ብለው ረዥምና ጥቁር ጦር ሰጡት:: ለንጊኖስ ወደ ጌታችን ዐይን ተመለከተ:: እያየው እንዳልሆነ ገመተ::
ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በባሕርይ ሥልጣኑ ለይቷልና ጦሩን ጨብጦ ወደ ጌታ ጐን ልኮ ወጋው:: ከጌታ ቀኝ ጐንም በ"ለ" አምሳል ትኩስ ደምና ውሃ ፈሰሰ:: አንዷ ፍንጣቂ ሔዳ የታወረች ዐይኑ ላይ ዐርፋ ዐይኑን አበራች::
ለለንጊኖስ ታላቅ ደስታ ሆነ:: ለእኛ ግን ማየ ገቦና ደመ ገቦ ፈለቀልን:: የጌታችን ትእግስቱና ቸርነቱ ግን ይደንቃል::
"ከመ ኢየሐስብ ቦቱ ዘኩናተ እዱ ርግዘቶ::
በኃጣውኢሁ ለዘኢፈቀደ ሞቶ::
ምሕረቶ እሴብሕ ወዐዲ ትዕግስቶ::" እንዳሉ ሊቃውንት::
ጌታችን ከተነሳ በሁዋላ ለንጊኖስ ወደ ቅዱስ ዼጥሮስ ዘንድ ሒዶ ስለ እውነት : ስለ ሃይማኖትም ተማረ:: ተጠምቆ: ምድራዊ ወታደርነቱን ትቶ እየሰበከ ከኢየሩሳሌም ወደ ቀዸዶቅያ ወረደ:: ለዘመናትም ጌታችን ክርስቶስን በሥርዓተ ወንጌል አገለገለ::
በመጨረሻም በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን አይሁድ አሳደዱት: አንገላቱት:: የነርሱ ወገን ስለነበረም መከራ አጸኑበት:: የጽድቅ አርበኛና የክርስቶስ ሐዋርያ ቅዱስ ለንጊኖስ ግን ጸና:: በዚህች ዕለትም አይሁድ አንገቱን ቆርጠውት ለሰማዕትነት በቃ:: ቅዱሱ በሕይወቱም በዕረፍቱም ተአምራትን ሠርቷል::
† እግዚአብሔር በቸር ጥሪው ሁላችንም ወደ ቀናው የጽድቅ ጐዳና ይጥራን:: ከሰማዕታቱም ረድኤት በረከት ይክፈለን::
† ሐምሌ ፳፫ [23] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩. ቅድስት መሪና እናታችን [ታላቋ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ለንጊኖስ ሐራ [ሐዋርያና ሰማዕት]
፫. ቅዱስ አብጥልማዎስ
† ወርኀዊ በዓላት
፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
፮. አባ ሳሙኤል
፯. አባ ስምዖን
፰. አባ ገብርኤል
† "ወደ ጌታ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም:: ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጐኑን በጦር ወጋው:: ወዲያውም ደምና ውሃ ወጣ:: ያየውም መስክሯል : ምስክሩም እውነት ነው:: እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ : እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል:: ይህ የሆነ:-
"ከእርሱ አጥንት አይሰበርም" የሚል የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው:: ደግሞም ሌላው መጽሐፍ:-
"የወጉትን ያዩታል" ይላል::" † [ዮሐ.፲፱፥፴፫] (19:33)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን":: /የቅዱሳንን ዜና [ታሪክ] እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
41 viewsባሕራን, 02:32