Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ጠዋት! ሰኔ 26/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት በስማቸው | EMS Mereja

ሰኞ ጠዋት! ሰኔ 26/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት በስማቸው ወይም በቅርብ ቤተሰባቸው የተመዘገቡ የንግድ ኩባንያዎችን ወይም የአክሲዮን ድርሻዎችን እንዲያቋርጡ ወይም ለሌላ አካል እንዲያስተላልፉ የሚያስገድድ ረቂቅ ደንብ መውጣቱን ሪፖርተር ዘግቧል። የባለሥልጣናትን የጥቅም ግጭት ማስቀረትን ዓላማው ያደረገውን ረቂቅ ደንብ ያዘጋጀው፣ የጸረ-ሙስና ኮሚሽን እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ኢንቨስትመንታቸውንና የግል ኩባንያቸውን በወኪሎቻቸው አማካኝነት እንዲመሩ፣ የኩባንያቸውን ካፒታልና ትርፍ በግል ማዘዝ በማይችሉበት የባንክ ሒሳብ እንዲያስቀምጡ ወይም በኩባንያዎች የያዟቸውን ከፍተኛ ሃላፊነቶች እንዲለቁ ያስገድዳል ተብሏል።

2፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የተመራ የቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በቅርብ ቀናት ውስጥ ወደ መቀሌ እንደሚጓዝ የቤተክርስቲያኗ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። የልዑካን ቡድኑ ጉዞ ዓላማ፣ የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ለክልሉ ለመስጠት የወሰነውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስና በትግራይ ከሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት ጋር "በሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር" እንደኾነ መምሪያው ገልጧል። በልዑካን ቡድኑ ውስጥ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው የሰላምና አቀራራቢ ኮሚቴ አባላት እንደተካተቱ መምሪያው ጨምሮ አመልክቷል።

3፤ ፌደሬሽን ምክር ቤት ነገ እና ከነገ ወዲያ በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ያካሄዱትን የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ለማጽደቅ እንደሚሰበሰብ መስማቱን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ምክር ቤቱ ውጤቱን የሚያጸድቀው፣ ምርጫ ቦርድ ዛሬ የሚያቀርብለትን የሕዝበ ውሳኔ ሪፖርት መሠረት በማድረግ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ወላይታ ዞንን ጨምሮ ስድስቱ ዞኖችና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች በሕዝበ ውሳኔው በከፍተኛ ድምጽ ከደቡብ ክልል ተነጥለው በጋራ አንድ ክልል ለማቋቋም መወሰናቸው ይታወሳል። አዲሱ ክልል "ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" ተብሎ እንደሚሰየም ይጠበቃል።

4፤ ሰሞኑን ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ጨምሮ ስድስት የአይኤስ የሽብር ቡድን አባላት ፑንትላንድ ራስ ገዝ ውስጥ ለመንግሥት ጦር እጃቸውን እንደሰጡ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። እጃቸውን ለመንግሥት ከሰጡት የቡድኑ ተዋጊዎች መካከል፣ አራቱ ኢትዮጵያዊያን እንዲኹም ሁለቱ ሱዳናዊያን እንደኮኑ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ተዋጊዎቹ በቡድኑ ተመልምለው ላንድ ዓመት ያህል ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ እንደቆዩ መናገራቸው ተገልጧል። ቡድኑ በተለይ ወደ ቦሳሶ ወደብ ለሥራ ወይም ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመሻገር የሚሄዱ የውጭ ዜጎችን ለምልመላ ዒላማ በማድረግ ይታወቃል።
ሼር ይደረግ


ለትክክለኛ ወቅታዊ መረጃዎች ቻናላችንን join በማድረግ ተከታተሉ
http://t.me/emsmereja