Get Mystery Box with random crypto!

ዜና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በጉራጌ ዞን በነዋሪዎች ላይ ግድያና እገታ እየፈጸሙ ነው ተባለ በደቡ | EMS Mereja

ዜና
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በጉራጌ ዞን በነዋሪዎች ላይ ግድያና እገታ እየፈጸሙ ነው ተባለ
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በተለይም ሶዶ ወረዳ፤ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራውና መንግሥት "ኦነግ ሸኔ" በሚል በአሸባሪነት የፈረጀው ኃይል በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ግድያና እገታ እንደሚፈጽም ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም የቡድኑ አባላት ነዋሪዎችን አግተው በመውሰድ አርደን የምንበላው ከብት ስጡን፣ የግል የጦር መሳሪያችሁን እንዲሁም ብር አምጡ በማለት በደል እንደሚፈጽሙ ተነግሯል።

ባለፈው ሃሙስ ሰኔ 22/2015 በነዋሪዎቹ ቤት በመግባት "የመንግሥት የጸጥታ አካላትን ትደብቃላችሁ እንዲሁም ያሉበትን ጥቆማ አልሰጣችሁንም" በሚል ነዋሪውን ሲያሰቃዩ እንደነበርና በዚህም ምክንያት አንድ የቀበሌው ነዋሪ የነበሩ አርሶ አደርን መግደላቸው ነው የተገለጸው።

የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው ከስድስት ወር በፊት ጀምሮ በተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱ ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ከባለፈው ሰኔ 20/2015 ጀምሮ ግን ግድያ እና እገታ እየፈጸሙ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ነዋሪዎችን አግተው በመውሰድ እስከ 200 ሺሕ ብር እንደሚጠይቁ በመጥቀስም፤ በአካባቢው (በቀበሌው) በቂ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባለመኖራቸው ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት ወደ ቀበሌው ዘልቀው የሚገቡት ከኦሮሚያ ክልል በመንግሥት የጸጥታ አካላት ሲሳደዱ መሆኑም ተጠቁሟል።

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው በጉዳዩ ላይ መረጃ እየተሰባሰበ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ሙሉ መረጃ ሲገኝ የምንገልጽ ይሆናል።" ገልፀዋል።
ሼር ይደረግ


ለትክክለኛ ወቅታዊ መረጃዎች ቻናላችንን join በማድረግ ተከታተሉ
http://t.me/emsmereja