Get Mystery Box with random crypto!

የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ለወደሙ ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ ምንም ዓይነት ድጋፍ እያደ | EMS Mereja

የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ለወደሙ ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ ምንም ዓይነት ድጋፍ እያደረገ አይደለም ተባለ

በትግራይ ክልል ለወደሙ ትምህርት ቤቶች በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ምንም ዓይነት ድጋፍ እየተደረገ አለመሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ በክልሉ ከኹለት ዓመት በላይ ሲካሄደው በነበረው ውጊያ በትምህርት ሴክተሩ ላይ ያደረሰው ውድመት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ፤ የዉድመቱ መጠንም መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ሆኖም የወደሙ ትምህርት ቤቶች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጠግኖ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር በፌደራል መንግሥት እስካሁን የተደረገ ድጋፍ እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም በትምህርት ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት በቃላት ለመግለጽ እጅግ አዳጋች ነው ካሉ በኋላ፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር ካልተረባረቡ አገሪቷ አሁን ካለችበት አቋም አንጻር ትምህርት ቤቶቹን ማደስ የማይታሰብ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት መጀመሩን ገልጸው፤ ይህም ከሚፈለገው ቁጥር አንጻር ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ተማሪዎች 24 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ተማሪዎች ቤት ከሚውሉ ይሻላል በሚል ባልተመሟላ የትምህርት ቁሳቁስ እየተማሩ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በጦርነቱ ወቅት የትምህርት ተቋማቱ የወደሙት ኢላማቸውን በሳቱ የጦር መሳሪያዎች ተመተው ሳይሆን፤ ሆነ ተብሎ ትምህርት ቤቶችን ለማውደም ድሮንን ጨምሮ የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም በደረሰባቸው ድብደባ ነው።

በተጨማሪም በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ስር ያሉ ትምህርት ቤቶች አሁንም በኤርትራ እና በአማራ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ "በእነዚህ አካባቢዎች በ100 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሁንም ድረስ ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ናቸው።" ብለዋል።

አክለውም ከጦርነቱ በፊት በክልሉ ከኹለት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደነበሩ በመግለጽ፤ በዚህ ወቅት ትምህርት እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች ቁጥራቸው ክ5መቶ ሺሕ አንደማይበልጥ አብራርተዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት በተማሪዎች፣ በመምህራን እንዲሁም በተማሪ ወላጆች ላይ የደረሰው ስነ ልቦናዊ ጉዳትም እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

       ሼር ይደረግ


ለትክክለኛ ወቅታዊ መረጃዎች ቻናላችንን join በማድረግ ተከታተሉ
http://t.me/emsmereja