"Trauma within drama" ኤልያስ ሽታኹን (የልደት ዳር ጨዋታ) ~ ~ ~ ~ ~ * ሞት ይመስለኝ ነበር ክፉ ነገር:: ለካ አሟሟት ነው:: አባቴን በፀብ እንደተኳረፍን አረፈ:: አላሳደግኝም:: ግን አልጎድለብኝም አልልም:: እንኳን አባት ጎረቤትም ያጎድላል:: ከሌላ ለወለዳቸው ታላላቆቼ ሁሉን ሆኖላቸዋል:: ልክ ነው :: እናት አልነበራቸውምና:: ሰዎች ውበቱን የሚናገሩልት በብዛት የሚቆጠር ሱፍ የነበረው:: ደረባባ:: ቢናገር የሚሰማ:: ቢቆጣ የሚፈራ:: እርቅ በእጁ ሽማግሌ ነበር:: እቃ የሚበርከትለት እንዲያውም "ቴፑ" 39 አመት እንደሰማባት ሲያወራ ሰምቻለሁ:: ሽቅርቅር ነው:: ቤት ከሱ የወሰድነው ነገር ብዙ ነው:: ውስጡን ለቄስ ውጪ ውበት:: ሰው የሚድር የራሱን ትዳር ያላቆመ:: የተበላሸ የሰው ልጅ መካሪ የራስ ልጅ ላይ ስነፍ:: ለሰው መሬት ለመግዛት ዋስ ለቤቱ ሩብ ካሬ የሌለው:: ብቻ እንደተጣላን ሞተ:: ለሊቱን ሙሉ ሲያጣጥር አይቸዋለሁ:: አጥንቱ ሲገተር ጥርሱ መግጠም ሲከብደው አይቸዋለሁ:: ጀምበር መውጫ ንጋት ላይ ነፍሱ ተለየችው:: ብቻዬን ከአስክሬኑ ጋ አለቀስኩ:: በብዙ ስሜት መሐል አንባሁ:: እንቀጠቀጣለሁ:: " ይቅር ብዬሀለሁ" ለማለት አቅም አለነበረኝም:: ህመሜን ስላልነገርኩት ንደድኩ እንጂ:: ቅያሜዬን በውል ሳላስርዳው ሞተ:: እውነቱን ሳልያስረዳኝ ሄደ:: እንድልጅ ሳይሆን እንደእኩያ አለቅስኩ:: እሱ አብሮኝ አይሁን እንጂ ስልሱ የማስበው አብሮኝ ኖሯልና:: እሱ እናቴ ላይ አጠፋ የምለውን እኔ ዛሬ ስንት ሴቶች ላይ አርጌ አየሁት:: ወንዶች አባቶቻቸውን ይርግማሉ:: ግን እንደአባቶቻቸው ናቸው:: ነገ የልጄ እናት እና ልጆቼ የሚወቅሱኝ እውንታቸውን ሳስብ የረገምኩትን አባቴን አዘንኩለት:: ግን ለመታረቅም ለመጣላትም መኖር ነበርበት:: በጊዜ ሂደት ታቦቴን የተነጥኩ መቅደስ ነፍሴን ይዤ እኳትናለሁ:: በምናገረው በምፅፈው ሁሉ ድሞ ምን አጣ ይሆን?ስል እረበሻለሁ:: እንማን ይቀብሉኛል? እንማን ይርቁኛል? "እኔ ቦታ የለኝም የቆምኩበት አያውቀኝም" እንዳለ ኪሩቤል:: ራሴን ለሰዎች ኖሬያለሁ ብልም ውሸት ነው:: ለምወዳቸው በሚል ሰበብ ለራሴ አልነበርም ወይ የኖርኩት:: ግጥምን ከድኜ ፂሜን ላጭቼ ፀጉሬን አንስቼ ድምፄን ዘግቼ ንባቤን ቀድጄ ስሜን አንስቼ ራሴን ሳየው የት አለሁ? በርግጥ ውሸት ብቻ አይደለንም:: እውነትም እንደዛው:: ቅልቅል መርዝ ነን:: ላንዱ መድኃኒት ላንዱ ገዳይ:: ተከታይ ካበጀን ወዲያ መልሰን የተከተለንን ጀሊል እንከተለዋለን:: እሱ ሚወደውን ለበሰን አውርተን አጊጠን እንታያለን:: የሚከተሉንን የመከተል ድራማ ላይ እንገባለን:: በ 14 አመቴ ይመለኛል:: እቤት ሽሮ በልተን ተኛሁ:: ወንድሜ ማታ አምሽቶ ሲመጣ ስጋ እጁ ላይ ነበር:: ሲጠበስ ሸተተኝ:: "ሁሉም በልተዋል" እናቴ "አዎ አንተ ብላ"ትለዋለች አቃተኝ:: እንደባነንኩ አስመሰልኩ:: ደነገጡ :: "ምነው?" "አባዬ ሲሞት አየሁ" እናቴ አማተበች:: ልተኛ ልመለሰ ወደትራስ መንገዴን ጀመርኩ:: "አቢ" ተጣራ ወንድሜ :: ጎሽ ብላ ሊሉኝ ነው:: "በል:: እንኳን ነቃህ ና ብላ" ያኔ በስራሁት ያኔ ተሰራሁ:: ድራማዬን ሰርቼ ስጋዬን በልቼ ተኛሁ:: "አልወደውም" በምለው ሰው ስም እንዴት ታሪክ ሰራሁ:: እንዴት? በስሙ በላሁ? በትንሹ ልቤ ሸረኛ ሆኜ ራሴን አየሁት:: የውነት ሞቷል ዛሬ:: ግን አልበላበትም:: ስሙንም አላነሳም:: ዛሬም አንስቼው ከሆነ አላውቅም.... 845 views15:46