Get Mystery Box with random crypto!

የአውሮጳ ሃገራት ሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው። ጀርመን ባ | ዶይቸ ቬለን | DW AMHARIC NEWS🇪🇹

የአውሮጳ ሃገራት ሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው። ጀርመን ባለፈው ሳምንት በርከት ያሉ ሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር አውላለች። ባለፈው ሳምንት አውሮጳ ውስጥ በተለይ ሕገ ወጥ የሰዎች ሽግግር የሚያከናውኑ በተበራከቱባቸው በአምስት ሃገራት ምርመራ ማካሄዱን ዩሮፖል አስታውቋል። በዚህም 39 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። ከመካከላቸው ሦስቱ ዋነኛ አቀነባባሪዎች መሆናቸውንም ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ በሙሉ የኢራቅ ዜጎች መሆናቸውን የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ ገልጿል። 18ቱ የተያዙት በቤልጅየም መንግሥት ጥያቄ ሲሆን ተላልፈው እንዲሰጧትም ጠይቃለች። ፈረንሳይም በበኩሏ ከሕገወጥ አሸጋጋሪዎቹ ተላልፈው ይሰጡኝ ያለቻቸው አሉ። የጀርመኗ ኦስናብሩክ ከተማ አቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ በዛሬው ዕለት እንደገለጹት ተፈላጊዎቹ ተጠርጣሪዎች ወደ የት ይላኩ የሚለው በውሳኔ ሂደት ላይ ነው። የተደራጁት በሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች ከጎርጎሪዮሳዊው 2021 አንስቶ ባሉት ጊዜያት 10,000 ገደማ ሰዎችን በእንግሊዝ ሰርጥ በኩል ወደ ብሪታንያ በፕላስቲክ ጀልባ አስገብተዋል ተብሏል። ይፋ በሆነው መረጃ መሰረትም ወደ ብሪታንያ በሕገወጥ መንገድ ከገቡት አብዛኞቹ የቪየትናም ዜጎች ናቸው። የጀርመን የዜና ወኪል የጠቀሰው የፖሊስ የውስጥ መረጃ እንደሚለው ጀርመን ውስጥ በተካሄደው አሰሳ በርካታ ገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ተገኝቷል። የፕላስቲክ ጀልባዎች እና በርካታ ሞተሮችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ጀርመን ውስጥ የተካሄደው አሰሳ ኦስናብሩክ እና ኖርድ ራይን ቬስትፋለን የሚካሄደውን ሕገወጥ የሰው ዝውውር መረጃ ያደረገ ነውም ተብሏል። እስካሁን በተገኘው መረጃ መሰረትም ጀርመን ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የሕገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች ቡድን ጀልባዎች እና ሞተሮችን የማቅረብ ኃላፊነት የያዘ መሆኑ ተደርሶበታል።