Get Mystery Box with random crypto!

... በተለያዩ ክልሎች የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መንግሥት ማስቆም አልቻለም | ዶይቸ ቬለን | DW AMHARIC NEWS🇪🇹

... በተለያዩ ክልሎች የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን መንግሥት ማስቆም አልቻለም ያሉ 10 ሲቪክ ማሕበራት ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲያስቆሙ ጠየቁ። ማሕበራቱ በደብዳቤው ባለፉት 4 ዓመታት ጥቃቶቹ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች መፈጸማቸውን አመልክተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ሰኔ 11፤2014፤ 338 ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት አስታወቋል። የአማራ ማህበር በአሜሪካ በበኩሉ ከ500 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ማረጋገጡን ገልጿል። ከቀናት በኋላም በቄለም ወለጋ መንገድ ሃያና ሮቢት ገበያ በተባሉ መንደሮች «ኦነግ ሸኔ» በተባለው ቡድን ታጣቂዎች ግድያ መፈጸሙን በርካቶች መፈናቀላቸውን፤ 50 የሚሆኑ ደግሞ ታፍነው መወሳደቸውን ደብዳቤው ዘርዝሯል።
ደብዳቤው «የአማራ ተወላጆች ጅምላ ግድያ» ያለው ተግባር በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ተነፍጎታል ሲል ይወቅሳል። የሸዋ ልማትና ሰላም ማሕበር በጎ ፈቃደኛ ሥራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፤ «የአማራ ክልል መንግሥት ከክልሉ ውጪ ያሉ አማሮችን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ ጠንካራ አቋምና ተቆርቋሪነት አያሳይም» ብለዋል።
የተባበሩት አማራ የበጎ አድራጎትና ልማት ማሕበር ፕሬዝደንት ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያበይን በበኩላቸው ደብዳቤው የተላከው «ችግሮች ከዛሬ ነገ ይሻሻላሉ የሚል እሳቤ ቢኖርም እየባሰ በመሄዱ» እንደሆነ ገልጸዋል። የተጻፈውም፣ ለተመድ የፀጥታው ም/ቤት፣ ለተመ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለተመድ ሰብአዊ መብት ጉባኤ፣ ለተመድ ሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ለአፍሪካ እና ለአውሮጳ ሕብረት፣ ለአምነስቲ ኢንተረናሽናል፣ ለሂውማን ራይትስ ዎችና ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መሆኑን ዓለምነው መኮንን ከባሕር ዳር በላከው ዜና ጠቅሷል።