Get Mystery Box with random crypto!

2.ጉባኤ ቁስጥንጥንያ ጉባኤው የተካሄደው በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ ነው፡፡ ምክንያት የሆነ መቅ | ደረጀ እና የድንግል ማርያም ልጆች ግሩፕ ቻናል።

2.ጉባኤ ቁስጥንጥንያ

ጉባኤው የተካሄደው በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ ነው፡፡ ምክንያት የሆነ መቅዶኒዮስ መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው በማለት ባስተማረው ትምህርት ነው፡፡ ይህ ክህደት ሲነሳ የቁስጥንጥንያ ንጉስ የነበረው ቴዎዶስዮስ ቀዳማዊ ይህ የቤተክርስቲያን ችግር በጉባኤ እንዲፈታ ባስተላለፈው መልእክት መሠረት 150 ሊቃውንት ተሰብስበዋል፡፡

በዚህ ጉባኤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የተወያዩባቸው መሠረታዊ ጉዳዮችም የሚከተሉት ናቸው::

1. መቅዶንዮስና ትምህርቱን ለማውገዝ

2.አቡሊናርዮስንና ትምህርቱን (በምሥጢረ ሥጋዌ ቃል እግዚአብሔር ሰው በሆነ ጊዜ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልተዋሃደም የሚለውን ክህደት) ለማውገዝ

3.ወልድ የተዋሃደው የአዳምን ሥጋ አይደለም ሌላ በቅድምና የነበረ ሥጋ ነው እንጂ የሚሉ መናፍቃንን ለማውገዝ፡፡

4.በኒቅያ ጉባኤ ላይ በተረቀቀው ጸሎተ ሃይማኖት ላይ የተጨመሩ

5ቱን የሃይማኖት ቀኖናዎችን ማርቀቅ

በዚህ ጉባኤ ላይ መቅዶንዮስ መንፈስ ቅዱስ ሕፁጽ፣ ፍጡር ነው ያለበትን ምክንያት ሲጠየቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ከዚህም በኋላ ጉባኤው በኢሳይያስ 6-3፣ በማቴዎስ 28-19 በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንድነትንና ሦስትነን በማስረዳት ቢነገረው ከኑፋቄው አልመለስም በማለቱ 150ው ሊቃውንት የክህደት ትምህርቱንና እርሱን አውግዘው ለይተውታል፡፡

ሌላው ጉባኤው የአቡሊናርዮስን በምሥጢረ ሥጋዌ ቃል እግዚአብሔር ሰው በሆነ ጊዜ ሥጋን እንጂ ነፍስን አልተዋሃደም የሚለውን የክህደት ትምህርት አውግዘዋል፡፡ ለዚህም በዮሐንስ 1-14 ላይ "ቃል ሥጋ ሆነ" የሚለውን በመጥቀስ በትክክል የቃልና የሥጋን ውህደትና መጽሐፍ ቅዱሳዊነት ሊቃውንት አስረድተዋል፡፡

ቅዱስ ጎርጎሪየስ ዘኢንዝናዙም ሰው ማለት ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን እንጂ ነፍስ አልነሳም ከተባለ ያዳነው ሥጋን እንጂ ነፋስን አይደለም ብሎ በመመለስ የአቡሊናርዮስን ክህደት ተናግሯል፡፡ ከዚህም በማያያዝ ጉባኤው በኒቅያ ጉባኤ አንቀጸ ሃይማኖት ከተጠቀሱት ተጨማሪ 5 አንቀጾችን አስቀምጧል፡፡ እነርሱም
1. በጌታ በአዳኝ ከአብ በሠረፀ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፣ እንስገድለት እናመስግነው

2. በሁሉ ባለች በሐዋርያት ጉባኤ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፡፡

3. ለኃጥያት ማስተሰርያ በምትሆን በአንዲት ጥምቀት እናምናለን

4. የሙታንን ትንሳኤ ተስፋ እናደርጋለን

5. የሚመጣውንም ሕይወት እንጠባበቃን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ይንን ከዚህ በላይ ያየነው በጉባኤ ቁስጥንጥንያ የረቀቀው አንቀጸ ሃይማኖት በኒቅያ ጉባኤ ከተወሰነው ጋር አንድ ሆኖ ዛሬም እኛ በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን  ሥር የምንኖር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የምናምነው የምንቀበለው አንቀጸ ሃይማኖት ነው።