Get Mystery Box with random crypto!

ካስያዙት የስራ ማስኬጃ ተጨማሪ የስራ ማስኬጃ ብድር ማግኘት ይችላሉ? ያስያዝነው 20% መዋጮ ለስ | Development Bank of Ethiopia (DBE) : Training to Lease Financing

ካስያዙት የስራ ማስኬጃ ተጨማሪ የስራ ማስኬጃ ብድር ማግኘት ይችላሉ?

ያስያዝነው 20% መዋጮ ለስራ ማስኬጃ ከተለቀቀ እና ካለቀ በኃላ በቀጣይ በሚኖረው የምርት ሂደት የስራ ማስኬጃ እጥረት ቢገጥመን ባንኩ የስራ ማስኬጃ ብድር ይሰጠናል ወይ? የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ እየተነሳ ይሰማል።

በመሠረቱ የስራ ማስኬጃ ተብሎ ደንበኛው ካስያዘው መዋጮ የሚለቀቀው ብር ድርጅቱ ወደስራ ለመግባት የሚያስችለውን መነሻ አቅም የሚፈጥርለት ነው። አቅም የፈጠረ እና ማምረት የጀመረ ድርጅት ደግሞ ለስራ ማስኬጃ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን በአብዛኛው ከድርጅቱ ምርታማነት እና ገቢ እንደሚያመነጭ ሳይንሳዊው የስራ ካፒታል አስተዳደር አስተምህሮ ያስቀምጣል። ይህም ማለት ያለ ሃብት (current assets) (ለምሳሌ በባንክ የተቀመጠ ብር ፣ ማስያዣዎች (securities)፣ በመጋዘን ያሉ ንብረቶች እና በ12 ወራት ውስጥ ወደጥሬ ገንዘብ የሚቀየሩ ተከፋዮች (receivables)) ድርጅቱ ካሉበት ዕዳዎች ማለትም ከሚከፈሉ ወጪዎች (ለምሳሌ ለጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች ፣ ለአከራዮች፣ ለውሃ፣ ለመብራት፣ ስልክ እና ወለድ የሚከፈል) እና በ12 ወራት ውስጥ መከፈል ካለባቸው ወጪዎች አንፃር በልጦ የሚገኝበት ሁኔታ እሙን ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ በቀላሉ አሁናዊ የፋይናንስ ግዴታዎቹን በራሱ ሊያሟላ እንደሚችል ይታመናል፡፡

ሆኖም ደንበኛው በዝግ አካውንት ገቢ ያደረገውን የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ተጠቅሞ ሲጨርስ ልላ የስራ ማስኬጃ ብድር ማግኘት ቢፈልግ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ ፖሊሲ LFP/002/2022 መሠረት ተከራዩ ተጨማሪ የስራ ካፒታል ብድር ከንግድ ባንኮች ወይም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዋስትና ሊበደር ይችላል። ባንኩ ይህንን መሰል የአጭር ጊዜ የስራ ካፒታል ብድር ሊሰጥ የሚችለው ደግሞ ከሁለት አመት የስራ ጊዜ በኋላ የድርጅቱ የስራ አፈጻጸም ደረጃ ታይቶ ነው።

⁂ ካስያዙት የስራ ማስኬጃ ተጨማሪ የስራ ማስኬጃ ብድር ማግኘት ይችላሉ?
»»»»» አዎ፣ የባንኩ የሊዝ ፋይናንሲንግ ፖሊሲ ያስቀመጠው መስፈርት እስከተሟላ ድረስ፡፡

በስልጠና ወቅት በአግባቡ እንደተገለፀው (ከስልጠናው ፓወር ፖይንት ቀጥታ ግልባጭ)፡-
1. ተከራዩ ተጨማሪ የስራ ማስኬጃ ካፒታል ብድር ከንግድ ባንኮች ወይም ከባንኩ በመያዣነት መበደር ይችላል።
2. ባንኩ ከሁለት አመት የስራ ጊዜ በኋላ የስራ አፈጻጸም ደረጃ ላላቸው ደንበኞች የአጭር ጊዜ የስራ ካፒታል ብድር ሊሰጥ ይችላል።