Get Mystery Box with random crypto!

ስለውርስ ህግ በጠቅላላውና የአወራረስ ስርዓት በኢትዮጵያ ======================== | Tsegaye Demeke - Lawyer

ስለውርስ ህግ በጠቅላላውና የአወራረስ ስርዓት በኢትዮጵያ
========================

1. ስለ ውርስ ህግ በጠቅላላው
በዓለማችን እየተሠራባቸው ያሉ ዘመናዊ የውርስ ህግጋት በመሠረታዊነት ሶስት አይነት የአወራረስ ሥርዓቶችን የሚዘረዝሩ የውርስ ደንቦችን የያዙ ናቸው፡፡ እነርሡም፣
የሟች ውርስ ያለኑዛዜ ለሟች የሥጋና የጋብቻ ዘመዶች የሚፈፀሙበትን የአወራረስ ሥርዓት በዝርዝር የሚደነግጉ፣ ደንቦችን የያዙ (Rules of Intestate Succession)
የሟች ውርስ በሟች ኑዛዜ መሠረት የሚፈፀምበትን ሥርዓት የሚደነግጉ ደንቦች የያዙ (Rules of testate Succession)
የሟች ውርስ በሟች በክፊል ኑዛዜና በከፊል ያለኑዛዜ የሚፈፀምበትን ደንቦች የያዙ (Rules of partially intestate and partially Testate secession) ናቸው፡፡
በአጠቃላይ አሁን እየተሠራባቸው ያሉ የውርስ ህግጋት የሟች የሚንቀሣቀሥ እና የማይንቀሣቀሥ ንብረት ገንዘብና ከሌሎች ሰዎች የሚሰበሰብ ብድር ወይም ተከፋይ ገንዘብ የአክስዮን ድርሻና ሌሎች በሟች መሞት ምክንያት የማይቋረጡ የሟች መብትና ግዴታዎች ለሟች ወራሾች ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚተላለፍበትን የአወራረስ ሥርዓት የሚደነግጉ ናቸው፡፡


2. የአወራረስ ሥርዓት በኢትዮጵያ

ስለ ኢትዮጵያ የአወራረስ ስርዓትና ህግ ስናነሳ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ያለውን የአወራረስ ስርዓት ነው፡፡
ህገ መንግስቱ የግል መብቶችን በተመለከተ የሚነሱ ክርክሮች በተከራካሪዎቹ ፈቃድ በባህላዊ ወይም ኃይማኖታዊ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብትን በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 ደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የሀይማኖት እና የባህል ፍርድ ቤቶችን ሊያቋቁሙ ወይም ዕውቅና ሊሰጡ እንደሚችሉ ከመደንገጉም በላይ ህገመንግስቱ ከመጽደቁ በፊት ዕውቅና አግኝተው ሲሰራባቸው የነበሩ የኃይማኖትና የባህል ፍርድ ቤቶች በህገመንግስቱ መሰረት በአንቀጽ 78 ንዑስ አንቀጽ 5 በግልጽ ደንግጓል፡፡ በዚህ መሰረት፣ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 188/1992 መሠረት ተጠናክሮ ስራውን የቀጠለ ሲሆን ክልሎችን የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን የማጠናከሪያ አዋጆችን በማወጅ ስራቸውን እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ስንመዝነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለበት ነሐሴ 1 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ባህላዊና ልማዳዊ የአወራረስ ደንቦች፣ ሀይማኖታዊ የአወራረስ ደንቦች ህገ መንግስታዊ ዕውቅናና ጥበቃ አግኝተው ከፍታብሔር ህጉ የውርስ ህግ ድንጋጌዎች ጐን በጐን እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የአወራረስ ስርዓቶች ስንመለከት ሁለት መሠረታዊ እና ልዩ ባህሪያት ያሉት ነው፡፡
የመጀመሪያው በእኩል ደረጃ ህገመንግስታዊ ዕውቅናና ጥበቃ በተሰጣቸው፣ 1)ባሕላዊና ልማዳዊ የውርስ አወራረስ ደንቦች 2)ሀይማኖታዊ የውርስ አወራረስ ደንቦች እና 3) በፍታብሔር ህጉ የተመለከቱት የተለያዩ አይነት ባህሪ እና ውጤት ያላቸው የአወራረስ ሥርአቶች በአገሪቱ ውስጥ ተግባራዊ እየሆኑ መሆናቸው ሲሆን፣
ሁለተኛው በሟች የውርስ አወራረስ ሒደት ሥርዓት ሲፈፀም የሚነሱ ክርክሮች ተፈፃሚነት ያላቸውን የአወራረስ ደንቦች የመምረጥ መብት ሙሉ በሙሉ የተከራካሪዎች መሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ መታየት ያለበት ከተከራካሪዎቹ አንደኛው በልማዳዊ ወይም ሀይማኖታዊ የአወራረስ ደንቦች መሰረት ለመዳኘት ፈቃደኛ ካልሆነ ጉዳዩ በፍታብሔር ህጉ የውርስ ህግ ድንጋጌዎች መሰረት የሚፈፀም መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡- ስለሆነም ዜጐች የፍታብሔር ህጉን የውርስ ደንቦች ተፈፃሚነት የሚያስቀሩት ጉዳዩ በባህላዊ ወይም ኃይማኖታዊ የአወራረስ ደንብ እንዲፈፀም ሙሉ በሙሉ ሲስማሙና ፈቃደኛ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡

የተለያየ አይነትና ባሕሪያት ውጤት ያላቸው የውርስ አወራረስ ደንቦች መኖራቸው ያለው ጠንካራና ደካማ ጐን
ከላይ እንደተገለፀው በአገሪቱ አንድ ወጥ የሆነ የአወራረስ ሥርዓት ኖሮ የማያውቅ ሲሆን አንድና ወጥነት ያለው የአወራረስ ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገው ሙከራም ተግባራዊ ውጤት አላስገኘም፡፡ ይህም በመሆኑና ህገመንግስቱ ባህልን፣ ሃይማኖትን መሰረት ለሚያደርጉ የአወራረስ ደንቦች ዕውቅናና ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ይህም ዜጐች በፈቃዳቸውና በፍላጎታቸው የህብረተሰባቸው ባህላዊ የውርስ ደንቦች ወይም ኃይማኖታዊ የውርስ ድንጋጌዎች መሰረት የሟች ውርስ የሚያስፈፅሙበት እድል የሚሰጥ በመሆኑ፣ ዜጐች የግል ጉዳያቸው በመረጡት መንገድ የመጠየቅና የመዳኘት መብታቸውን ያረጋግጣል፡፡ ይህም ሊመሰገን የሚገባው ጠንካራ ጎን እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ከአንድ በላይ የሆኑ የውርስ አወራረስ ስርዓቶች በአንዲት አገር ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከር የአንዱ የአወራረስ ሥርዓት ደንቦች ከሌላው የሚለያዩበት ሰፊ ሁኔታ ስለሚኖርና ከሚች ወራሾች መካከል የተወሰኑትን በአንደኛው የአወራረስ ስርዓት ሌሎቹ ደግሞ በሌላ የአወራረስ ሥርዓት መሰረት የሟች ውርስ እንዲፈፀም ለማድረግ የየበኩላቸውን ጥያቄ ስለሚያቀርቡና በሌሎች ምክንያቶች የሚፈጠረው የተለያዩ የውርስ ደንቦችና የአፈፃፀም ግጭት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ተፈፃሚነት ያላቸው ባህላዊ የአወራረስ ሥርዓቶች ብዛታቸውን፣ ይዘታቸውን የሚያሳይ ወጥ ጥናት ባለመደረጉ በእርግጠኘነት ብዛታቸውን፣ ይዘታቸውንና የአፈፃፀም ሒደታቸውን ከሌሎች ኃይማኖታዊና የፍታብሔር ህግ የውርስ ድንጋጌዎች ጋር በማነፃፀር ለመግለጽ አይቻልም፡፡ ሆኖም የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ጎሳዎችና ማህበረሰቦች የየራሳቸው ባህላዊ የውርስ አወራረስ ደንቦች እንዳላቸውና እነዚህም በይዘትም ሆነ በአፈፃፀም የተለያየ ይዘትና ባህሪ እንዳላቸው በተለያየ ጊዜ ከተደረጉ አጫጭር የዳሰሳ ጥናቶች ለመረዳት ይቻላል፡፡

ስለሆነም በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆኑ ባሉ የባህል አወራረስ ደንቦች መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት እንደዚሁም እያንዳንዱ ባህላዊ የውርስ አወራረስ ሥርዓት እየተሰራባቸው ካሉት የፍትሐብሔር ህጉ እና የሸሪዓ የውርስ ድንጋጌዎች ያላቸውን አንድነት እና ልዩነት በንጽጽር ለማቅረብ አይቻልም፡፡ በአንጻሩ ጐን በጎን የሚተረጉሟቸው እና የሚያስፈጽሟቸው ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው እየተሰራባቸው ባሉት የፍትሐብሔር ሕግ የውርስ ደንቦችና በሸሪዓ የውርስ ደንቦች መካከል ያለውን መሰረታዊ የይዘት ልዩነትም በአፈፃፀም ሒደት እየተከሰቱ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች ማየት በአገራችን የተለያዩ ባህላዊ ኃይማኖታዊና የፍትሐብሔር ህግ የተደነገገውን የአወራረስ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ሒደት ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ለመረዳት ጠቀሜታ ስለሚኖረው በአጭሩ ማየት ይጠይቃል፡፡

የሸሪዓና የፍትሐብሔር የውርስ ደንቦች መካከል የሚታየው መሠረታዊ ልዩነትና በአፈፃፀም የሚታዩ ችግሮች