Get Mystery Box with random crypto!

ባንኮችም የዋስትና ሰነድን ለደንበኞች በመስጠት የሚያገኙት ገቢ በወለድ መልክ ገንዘብን መቀበልንና | Tsegaye Demeke - Lawyer

ባንኮችም የዋስትና ሰነድን ለደንበኞች በመስጠት የሚያገኙት ገቢ በወለድ መልክ ገንዘብን መቀበልንና የዋስትና ጊዜው ሲያልቅ የሚመለስ ገንዘብም በዋስትና ተጠቃሚው በኩል እንዲከፈል አይጠበቅም። በመሆኑም የዋስትና ሰነድ መጻፍ በተለምዶ የሚታወቀውን የአበዳሪና ተበዳሪ የብድር ግንኙነትን አይፈጥርም። ይልቁንም ባንኮቹ ለሚሰጡት የዋስትና ሰነድ የሚቀበሉት ተመጣጣኝ የሆነ ኮሚሽን ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ ታዲያ በተለይ የዋስትና ሰነድ እንደ ብድር አገልግሎት የሚታይ አይደለም ለሚሉት ወገኖች እንደ አንድ መከራከሪያ ሀሳብ ይነሳል። ምክንያቱም የባንክ የብድር ግንኙነት የአበዳሪና የተበዳሪ ግንኙነትን ለመፍጠር አበዳሪው ለተበዳሪው በገንዘብ የሆነ ብድር የመስጠትንና ተበዳሪውም ይህንኑ የብድር ገንዘብ በዓይነትም ሆነ በጥሬው የመመለስ ግዴታን የሚጥል መሆኑ ግልጽ ነው።ይሁንና ግን የዋስትና ደብዳቤ ለዋስትና ተጠቃሚው ሲጻፍ ባንኮቹ የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት የጠየቀውን ደንበኛቸው የገባውን ግዴታ እንዲፈጽም መተማመኛ ከመስጠት ባለፈ ለደንበኛቸው የሚሰጡት የብድር ገንዘብ የለም።

ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ባንኮች በሚያዘጋጂዋቸው የዋስትና ደብዳቤዎች ላይ የሚጠቀሱ የሰነዱን ይዘቶች የተመለከቱት ነጥቦቸ ናቸው። በተግባር በባንኮች የሚዘጋጁት የዋስትና ሰነዶች የተለያዩ ቢሆኑም የሰነዶቹ ይዘት ግን አንዳንድ የሕግ ክርክሮችን ሲያስነሱ ይታያሉ።የአንዳንድ የዋስትና ደብዳቤዎች ይዘቶች በተለይም ዋስትና ሰጪውን ተቋም ሳይቀር ባለገንዘቡ የዋስትና ሰጪው እና ወራሾቹ በጋራም ሆነ በተናጠል በደብዳቤው በተቀመጡት ግዴታዎች መሠረት ራሳቸውን ህጋዊ ግዴታዎች ውስጥ ገብተዋል፤ የዋስትና ቦንዱም ለተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በቦንዱ ውስጥ በሰፈሩት ህጋዊ ስምምነቶች እና ድንጋጌዎች መሠረት ሆኖ ይህንን ቦንድ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይችል የሚያደርጉ ናቸው፤ ማንኛውም ድርጊት ወይም ሳይፈጸም የቀረ ነገር በመኖሩ ሳቢያ ኪሳራ የሚደርስ መሆኑን ዋስትና የተሰጠው ባለገንዘብ ከደረሰበት ይህንኑ በዋስትና ጊዜው ውስጥ ለዋሱ ማሳወቅ አለበት የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በመሠረቱ አንዳንዶቹ ግዴታዎች በልማድ የተጻፉ ከመሆናቸው ውጪ በተለይ የዋሱን ወራሾች ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉት የዋስትና ግዴታዎች ባንኮችን በተመለከተ ሊፈጸሙ የሚችሉም ስላልሆኑ በአብዛኛው በሰነዶቹ ይዘት ላይም ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል። የዋስትና ደብዳቤም በጊዜ ገደብ የተወሰነ ግዴታ ሲሆን ደብዳቤውም በግልጽ ዋስትና የተገባለትን የገንዘብ መጠን ማመልከት ይገባዋል።

እንደማጠቃለያም የዋስትና ውል ማለት ሁለት ሰዎች ባደረጉት የባለገንዘብነትና የባለእዳነት ግዴታ ግንኙነት ውስጥ ከእነዚህ ተዋዋዮች ውጪ የሆነ ሌላ ሦስተኛው ባለእዳው እዳውን በሙሉ ወይም በከፊል ያልተከፈለ መሆኑ ከተረጋገጠ ወይም ግዴታውን በውሉ በተመለከተው አኳኋን በአግባቡ ያልተወጣ ከሆነ እኔ በባለእዳው ስፍራና አቋም ሆኘ እዳውን እከፍላለሁ ወይም ግዴታውን እወጣለሁ ሲል ለባለገንዘቡ ማረጋገጫ የሚሰጥበት በሕግ አግባብ ከተረጋገጠ ከበስተጀርባው ለአፈጻጸሙ የሕግ ጥበቃ የሚያገኝ ውል ነው በማለት የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ማብራሪያ ሰጥቷል። ይሁንና ግን የዋስትና ሰነዶች ከአገልግሎታቸው አንጻር በህጋችን ላይ ግልጽና ሰፊ ሽፋን የተሰጣቸው አይደሉም። በተለይም በንግድ ሕጉን ውስጥ እነዚህ ሰነዶች እንደ ብድር አገልግሎት የሚቆጠሩ መሆንና አለመሆናቸውን በሚገልጽ መልኩ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት የዋስትና ደብዳቤዎችን አገልግሎት እና በምን ሁኔታ ሊጻፉ እንደሚችሉ በሚገልጽ መንገድ የተቀመጠ ግልጽ ድንጋጌ ያስፈልገናል። በመሆኑም የንግድ ሕጉ የዋስትና ደብዳቤዎችን የተመለከተ ሰፊ የሕግ ሽፋን መስጠትና ማካተት ይጠበቅበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የዋስትና ሰነዶችን ልዩ ባህሪያትና በተግባር ያሉትን የባንኮችን አሰራሮች በመፈተሽ ዝርዝር የሕግ ድንጋጌ ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው።
By Abyssinia Law