Get Mystery Box with random crypto!

መሠረት የዋስትና ደብዳቤን ለማዘጋጀት በአብዛኛው የሚቀርበው የመያዣ ንብረት በመሆኑና የሰው ዋስትና | Tsegaye Demeke - Lawyer

መሠረት የዋስትና ደብዳቤን ለማዘጋጀት በአብዛኛው የሚቀርበው የመያዣ ንብረት በመሆኑና የሰው ዋስትና በፍትሐብሔር ሕጉ በተቀመጠው መሠረት የዋስትና ደብዳቤ ለመጻፍ እንደመያዣ የማይቀርብ በመሆኑ በሰው ዋስትናና በሰነዶች ዋስትና መካከል መሠረታዊና ሰፊ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል ማለት ነው። በመሆኑም ይህ የዋስትና አገልግሎት በዋናነት ሰውን እንደዋስትና ወይም እንደ መያዣ ማቅረብን የሚመለከት አይደለም። ለዚህም ይመስላል የፍትሐብሔር ሕጉ ራሱ የሰው ዋስትናን እንደ አንድ የዋስትና ዓይነት በዘረዘረበት የሕጉ ድንጋጌዎች አሁን ባንኮች የሚጠቀሙባቸውን የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና፣ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ደብዳቤዎችንና ሌሎችንም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሠረት አድርገው እና ለተለያዩ ዓላማ የሚውሉትን የዋስትና ዓይነቶችም ቢሆን ለመዘርዘር ያልቻለው።

በሀገራችን በተለይም እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች በአለም አቀፍ ደረጃም በተገባር ላይ መዋል የጀመሩትና ይህ ልማድም ወደ ሀገራችን ገብቶ በባንኮች መተግበር የጀመረውም የንግድ ሕጉና የፍትሐብሔር ሕጉ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የዋስትና ሰነዶን በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጉን መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችም ሆነ የሕግ ትርጉሞች በመሠረታዊነት እነዚህ በባንኮች በአገልግሎት ላይ የሚውሉ የዋስትና ሰነድ ዓይነቶችን የማይወክሉ የሚሆኑት። በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የዋስትና ሰነዶችን በተለይም (Independent Letter of Guarantees) በተመለከተ በኮድ መልክ የወጣውና በአብዛኛው ሀገሮችና ተቋማት አገልግሎት ላይ የሚውለው URDG 458 የሚባለው ሰነድ ሲሆን ሰነዱም ከጥቂት አመታት በኋላ URDG 758 በሚል ተሻሻሎ ቀርቧል። ስለዚህም የዋስትና ሰነዶች ታሪካዊ አመጣጥና በተግባር አገልግሎት ላይ መዋል የጀመሩትም የኢትዮጵያ የፍትሐብሔርና የንግድ ሕግ ከወጡ በኋላ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ 47004 በተሰጠ አስገዳጅ የሕግ ውሳኔ መሠረት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና ውል በፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት የሚገዛ መሆኑን ገልጿል። ሰበር ችሎቱ በርካታ ትንታኔዎችን በጉዳዩ ላይ ለመስጠት የተጓዘበት ርቀት ጥሩ የሚባል ቢሆንም በመሠረታዊነት ግን ውሳኔው ሁሉንም የሕግ ባለሙያ ሊያስማማ የሚችል አይመስልም። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በውሳኔው ላይ የዋስትና ሰነድን የዋስትና ውል ሲል የገለጸው ሲሆን ከላይ በተመለከትነው መሠረት ግን ሰነዱ በባንኮች ተዘጋጅቶ የዋስትና ተጠቃሚውም ሆነ አበዳሪው በዚህ ሰነድ ላይ ምንም ዓይነት የስምምነት ፊርማ ሳያስቀምጡ፤ እንደሌሎች ውሎችም ምስክሮች መኖርም ሆነ መፈረም ሳያስፈልጋቸው በባንኮቹ ብቻ ተፈርመው ለዋስትና ተጠቃሚው የሚሰጡ ሰነዶች ናቸው።

በመሆኑም በዚህ ሰነድ ላይ እንደውል ለመቆጠር ቢያንስ ሁለት ወገኖች በውሉ ስለመስማማታቸው በጽሑፍ በሆነ ሰነድ ላይ መፈረምና ምስክሮችም ስማቸውንና ፊርማቸውን ማስቀመጥ እንደሚገባቸው የውል ሕግ እያስገደደ እነዚህ ነጥቦች ባልተሟሉበት ሁኔታ ሰነዱን ውል ማለት መሠረታዊ የውል መርህን የሚጥስ ነው። ሌላው የሰበር ትንታኔው የዋስትና ውል ብሎ የጠራውን ሰነድ በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 1920 እስከ 1951 የተቀመጠ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና ውል በችሮታ ላይ የተመሠረተ ግዴታ መሆኑን በመግለጽ ዋሱ ዋስ በመሆኑ የሚያገኘው ጥቅም የሌለ በመሆኑ አንድ ሰው ባለእዳው ሳይጠይቅ ወይም ሳያውቅ ዋስ መሆን እንደሚችል መመልከቱ ግንኙነቱ የግድ ጥቅም ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን የሚያሳይ ነው በሚል ያስቀመጠው ነው። (የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 921ን ይመልከቱ) ይህ ትንታኔም በአንድ በኩል የሰው ዋስትናን ከሰነድ ዋስትና ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ይመስላል። ይሁንና ስለሰው ዋስትና የተቀመጠው ይህ ትንታኔ በምንም መልኩ የሰነድ ዋስትናን የሚወክል አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ በባንኮችም ሆነ በኢንሹራንስ ድርጅቶች የሚሰጡ የሰነድ ዋስትናዎች እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በችሮታ የሚሰጡ ሳይሆን በተለይ ባንኮች የሰነድ ዋስትናዎችን ለመጻፍ ከተጠቃሚው ጋር የንብረት ወይም የገንዘብ መያዣ ውል የሚገቡ ሲሆን የዋስትና ሰነዶቹንም ለተጠቃሚው የሚጽፉት የዋሰትና መጠኑን መሠረት አድርገው በሚቀበሉት የገንዘብ ኮሚሽን እንጂ በችሮታ አለመሆኑ ነው።

ችሮታም የሰው ዋስትና መሠረታዊ መለያ ባህሪ እንጂ ለሰነዶች ዋስትና የሚሰራ ጉዳይ አይደለም። የሰነድ ዋስትና ለመጻፍም ባለእዳው ሳያውቅ መጻፍ የማይቻል ሲሆን የሰነድ ዋስትናን ለመጻፍ የግዴታ ባለእዳው በአካል ቀርቦ ለባንኩ ማመልቻ ማስገባትና ለሰነዱ መጻፍ መሠረት የሆነውን የመያዣ ውል መዋዋል ግድ የሚል ነው። በመሆኑም የሰነድ ዋስትና ለመስጠት የባለእዳው መቅረብና ስለዋስትናው ማወቅ የግድ ነው። በሌላ በኩል ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የዋስትና ሰነድ የፍትሐብሔር ሕጉ ከወጣ በኋላ የመጣ ጽንሰ ሀሳብ በመሆኑ ይህንን ግዴታ ወደፍትሐብሔር ሕጉ ወስደን ትርጉም ለመስጠት መሞከሩ አግባብ ያልሆነ መሆኑ ነው። በመሆኑም የሰበር ችሎቱ የሰነድ ዋስትናን ከሰው ዋስትና ጋር ለማዛመድ የሞከረበት ትንታኔው ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተቀባይነት ያለው አይመስልም።ይህ የሚያመለክተንም በመሠረቱ እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች በልማድ ባንኮች በተግባር በሰፊው ይጠቀሙባቸው እንጂ አገልግሎታቸው ተለይቶ እንዴት እንደሚዘጋጁ እና በምን ሕግ እንደሚገዙም የሚገልጽ ግልጽ የሕግ ደንጋጌ አሁን ባሉት የንግድ ሕግም ሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ የሌለ መሆኑን ነው።

የዋስትና ሰነዶች በሁኔታ ላይ የተመሠረቱና በሁኔታ ላይ ያልተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ዋስትና የሚባለው ዋሱ ባለዕዳው ግዴታውን በማንኛውም ሁኔታ ሳይወጣ ቢቀር ግዴታውን ያልተወጣው በምንም ምክንያት ይሁን ምክንያቱን መጠየቅ ሳይጠበቅበት የተባለው ግዴታ እንዳልተፈጸመ በአበዳሪው ሲገለጽለት በዋስትና ደብዳቤው የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆኑን በማረጋገጥ የሚከፈሉ የዋስትና ደብዳቤዎች ናቸው። በሁኔታ ላይ የተመሠረቱ የዋስትና ደብዳቤዎች ደግሞ ዋሱ ለአበዳሪው የዋስትና ግዴታውን ለመወጣት እንዲያስችለው ባለአዳው (ዋስትና የተገባለት ሰው) ግዴታውን ያልተወጣው በማን ጥፋት ነው የሚለውን ካረጋገጠ በኋላ እና ጥፋቱ የባለእዳው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የሚወጣው ግዴታ ነው።

ባንኮች በአሁኑ ወቅት እየሰጡዋቸው ካሉ የዋስትና ሰነድ ዓይነቶች ውስጥ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና፣ የቅድመ ክፍያ ዋስትና፣ የአቅራቢነት ዋስትና ሰነዶች (ደብዳቤዎች) ናቸው። እነዚህ የዋስትና ሰነዶች በአብዛኛው ባንኮች ለደንበኞች የሚያዘጋጁላቸው ደንበኞች ለባንኮች በሚያቀርቡት የመያዣ ንብረቶች መሠረት የመያዣ ውል ከተዋዋሉ በኋላ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት የጠየቀ የባንክ ደንበኛን ባንኮቹ ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ በዝግ ሂሳብ እንዲያስቀምጡ በማድረግ በምትኩ ግዴታቸውን ለመወጣት መተማመኛ የሚሆኑ ሰነዶችን ይሰጣሉ። ይህ ዓይነቱ ዋስትና የገንዘብ ዋስትና ይባላል። በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር sib/24/2004 መሠረት የገንዘብ ዋስትና ሰነድ አንድ ሰው አንድን የተለየና የተወሰነ ሥራ ለሌላ ሰው ለመሥራት ግዴታ ከገባ ይኸው ሰው በውሉ መሠረት የገባውን ግዴታ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ሰው የሚያቀርበው ውል ነው።