Get Mystery Box with random crypto!

የባንክ ዋስትና ሰነዶች (Letter of Guarantees) በኢትዮጵያ ሕግ ያላቸው ሽፋን ===== | Tsegaye Demeke - Lawyer

የባንክ ዋስትና ሰነዶች (Letter of Guarantees) በኢትዮጵያ ሕግ ያላቸው ሽፋን
=====================
የዋስትና ሰነዶች ባንኮች በተለይም ለደንበኞቻቸው ከሚሰጧቸው የብድር አገልግሎቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። የዋስትና ሰነዶች በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሩ ሲሆን በዚህም መሠረት በእንግሊዝኛ ‘independent undertakings’, ‘performance bonds/guarantees’, ‘tender bonds/guarantees’, ‘independent (bank) guarantees’, ‘demand guarantees’, ‘first demand guarantees’, ‘bank guarantees’, and ‘default undertakings’ በሚሉ ስሞች ሊጠሩ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም እነዚሁ ሰነዶች ‘standby Letters of Credit’ ተብለው ሊጠሩ እንደሚችሉ የተለያዩ ጽሑፎች ያሳያሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥም የዋስትና ሰነዶች የሚለው ጥቅል ስያሜን ለመጠቀም የተሞከረ ሲሆን አንዳንዶቹ ስያሜዎችም የዋስትና ዓይነቶችን የሚያመለክቱ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የዋስትና ሰነዶች በባንኮች የሚሰጡት ደንበኞች የተለያዩ ስምምነቶችን ከሌሎች ሦስተኛ ወገኞች ጋር ፈጽመው ያለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ለመወጣታቸው ከባንኮች ዋስትና እንዲሰጥላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ነው። የዋስትና ደብዳቤ የሚሰጠውም አንድን ሰው የብድር አገልግሎት ወይም እቃዎቸንና አገልግሎቶችን ለሌላ ሦስተኛ ወገን በብቃት እንዲያቀርብ መተማመኛ በመሆን ነው። ዋስትና ሰነድም አንድ ሰው አንድን የተለየና የተወሰነ ሥራ ለሌላ ሰው ለመሥራት ግዴታ ከገባ ይኸው ሰው በውሉ መሠረት የገባውን ግዴታ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ሰው የሚያቀርበው ውል ነው። (የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር መዝገብ ቁጥር 47004 ተመልከቱ) የዋስትና ሰነዶች የባንክ የብድር ዓይነቶች ወይም የብድር አገልግሎት መሆናቸውን ከማየታችን በፊት ግን የዋስትና ሰነዶች ምን ማለት እንደሆኑ ማየቱ ተገቢነት ይኖረዋል።
የዋስትና ደብዳቤ አንድ ደንበኛ የፈለገውን የንግድ እንቅስቃሴዎችና ግንኙነቶችን እንዲፈጽም ለማስቻል ደንበኛው ለአቅራቢው ወይም የአገልግሎት ተግባር ለመፈጸም የተዋዋለውን ደንበኛ ሥራውን እንዲያከናውን ለማስቻል የሚሰጥ ደብዳቤ ሲሆን የዋስትና ደብዳቤውን የሚያዘጋጀው ባንክም ሰነዱ የተዘጋጀለት ደንበኛ ግዴታውን መወጣት ባይችል ለተጠቃሚው በቀጥታ ግዴታውን እንደሚወጣ በማረጋገጥ የሚዘጋጅ ነው። የዋስትና ሰነዶችን በተመለከተ የሕግ ሽፋን የሰጠው የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን (UN Convention on Independent Guarantees and Standby Letters of Credit) የዋስትና ደብዳቤ ምን ማለት እንደሆነ እና የዋስትና ደብዳቤ ዓይነቶችንም ለመዘርዘር ሞክሯል። በዚሁ አለም አቀፍ ሕግ መሠረትም የዋስትና ደብዳቤ በአዘጋጁ (በብዛት ባንኮች ሲሆኑ) ደብዳቤው ለተዘጋጀለት ተጠቃሚ ዋስትና የተገባለት ግዴታ በባለዕዳው የማይከፈል ቢሆን የዋስትና ደብዳቤውን የጻፉት ባንኮች ባለዕዳውን ተክተው ክፍያውን (ዕዳውን) ለመክፈል ዋስትና እንደሚሆኑ በመግለጽ የሚሰጥ ደብዳቤ ነው። ይሁንና ይህ ኮንቬንሽን የሚያገለግለው አለም አቀፍ የሆኑ ግብይቶችን በተመለከተ እንደሆነ ተገልጿል። ኮንቬንሽኑንም የፈረሙት ሀገሮች ጥቂት በመሆናቸው ሁሉም ሀገሮች በዚህ ስምምነት መሠረት ይዳኛሉ ባይባልም አብዛኛው ሀገራት ግን የዋስትና ሰነዶችን በተመለከተ በሚያወጧቸው ሕጎች የዚህን ስምምነት አንቀጾች ከግንዛቤ በመክተት ሊሆን ይችላል። ኮንቬንሽኑ በተለይም የተለያዩ ዓይነት የዋስትና ደብዳቤ ዓይነቶች እንዳሉ ደንግጓል።

በኢትዮጵያ ሕግ ከዋስትና ሰነዶች ጋር በተያያዘ መነሳትና መዳሰስ ካለበት ዋና ነጥቦች መካከል የዋስትና ደብዳቤ ምን ማለት እንደሆነ፤ የዋስትና ደብዳቤ ምን ምን ነገሮችን ማካተት እንዳለበት፤ የዋስትና ደብዳቤዎች ያላቸው ሕጋዊ አስገዳጅነት፤ የዋስትና ሰነዶች ከሌሎች የዋስትና ዓይነቶች (እንደ ሰው ዋስትና እና የንብረት ዋስትና) ጋር ያላቸው አንድነት እና ልዩነት፤ እንዲሁም የዋስትና ሰነዶች እየተሰራባቸው ካለው ልማዳዊ አሰራር መነሻ ያደረገ ሌላ ሕግ አስፈላጊነት እና የመሳሰሉት ነጥቦች መብራራት ያለባቸው ናቸው።


ዋስትና የገንዘብ፣ የሰው እንዲሁም የንብረት እና የሰነድ ዋስትና ሊሆን ይችላል። እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች ግን በየራሳቸው ልዩነት ያላቸው ሲሆን ሁሉንም በተመሳሳይ መልኩ ትርጉም በመስጠት ወይም አንዱን በአንዱ እያቀያየርን መጠቀም በመደረታዊነት ያሉትን የተለያዩ የዋስትና ዓይነቶች እና ያላቸውን ጠቀሜታ የሚያጠፋ ይሆናል። በዋናነት በንብረት፤ በሰው እና በሰነድ ዋስትና መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ የፍትሐብሔር ሕጉን ድንጋጌዎች መመልከት ያስፈልጋል።

የፍትሐብሔር ሕጉ የሰው ዋስትናን (Suretyships or Guaranteership) በተመለከተ ከአንቀጽ 1920 እስከ 1951 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። እነዚህ የሕጉ ድንጋጌዎች ግን የሚገለጹት ስለ ሰው ዋስትና ሲሆን በዚህም መሠረት ግለሰቦች ራሳቸውን ለአንድ ብድር ዋስትና አከፋፈል ባለዕዳው በገባው ውል መሠረት ግዴታውን መፈጸም እንዲችል ለማረጋገጥ የሚሰጡት ዋስትና ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ የተገለጹት ዋስትናን የተመለከቱት ድንጋጌዎች ከውል ሕግ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው የባንክ የብድር ግንኙነቶችን አስመልክቶ በባንክ የሚዘጋጁትን የዋስትና ደብዳቤዎችን የማይወክሉና የማይመለከቱ ናቸው። በባንክ የሚዘጋጁት የዋስትና ደብዳቤዎች በባንኮች ከመዘጋጀታቸው በፊት ዋስትና ደብዳቤው እንዲዘጋጅለት የጠየቀው ደንበኛ የዋስትና ደብዳቤውን ከማግኘቱ በፊት ለደብዳቤው መሠረት የሆኑ ሁለት ዓይነት የተለያዩ እና በራሳቸው የቆሙ ውሎችን ይዋዋላል። አንደኛው ውል የዋስትና ደብዳቤው እንዲዘጋጅለት የጠየቀው ሰው ሊፈጽመው የገባው የአገልግሎት ወይም የአቅርቦት ወይም ሌላ ግዴታን የተመለከተና ከሦስተኛ ወገን ጋር የሚገባው ውል ነው። ሁለተኛው ውል ደግሞ የዋስትና ደብዳቤውን ከባንክ እንዲፈቀድለት የሚጠይቀው ሰው ከባንኩ ጋር የሚገባው ውል ነው። ይህ ውል የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት ጥያቄ ያቀረበው ሰው ደብዳቤው በባንኩ እንዲጻፍለት ባንኩ የሚጠይቀውን ዓይነት ዋስትና ማለትም የንብረት ወይም የጥሬ ገንዘብ ዋስትና በማቅረብ የሚዋዋለው የመያዣ ውል ነው። እነዚህ ሁለት ውሎችም እርስ በእርሳቸው የማይገናኙ እና በራሳቸው የቆሙ ናቸው ማለት ይቻላል። የዋስትና ደብዳቤው ደግሞ ከእነዚህ ውሎች በኋላ በባንኮች የሚሰጥ የዋስትና ሰነድ ሲሆን ይህንን በባንኮች ተዘጋጅቶ ለባለእዳው የሚሰጠውን ደብዳቤ ግን እንደ ውል ልንቆጥረው የምንችለው ሳይሆን በቅድሚያ ባንኮች እና የዋስትና ሰነዱን የጠየቀው ሰው በገቡት የመያዣ ውል አማካኝነት የሚዘጋጅ ደብዳቤ እንደሆነ የሚቆጠር ነው።

በመሆኑም የዋስትና ደብዳቤው የሚዘጋጀው በባንኮች በመሆኑና በደብዳቤው ላይ የሚፈርመውም የሚያዘጋጀው ባንክ ብቻ በመሆኑና የዋስትና ደብዳቤው ላይ ዋስትና የተገባለት ሰውም ፊርማውን የማያኖር ሲሆን በደብዳቤው ላይም የምስክሮች ፊርማም ሆነ ስም በአብዛኛው አይቀመጥም። በመሆኑም ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ደብዳቤውን ውል ለማለት የውል መሠረታዊ ሁኔታዎችን ያላሟላ መሆኑን ሲሆን ውል ነው የምንል ቢሆን እንኳን ከራስ ጋር የተደረገ ውል እንደሆነ ከመቆጠር ውጪ ሌሎች ውሎች የሚያሟሉትን ነጥቦች የሚያሟላ አይደለም። በዚህም