Get Mystery Box with random crypto!

የወንጀል ህግ ምንነት፣ ዓላማውና ህገ መንግስቱ ==================== የሰው ልጅ ሠላማዊ | Tsegaye Demeke - Lawyer

የወንጀል ህግ ምንነት፣ ዓላማውና ህገ መንግስቱ
====================
የሰው ልጅ ሠላማዊ ህይወትን ለመምራት ከወንጀል የፀዳ ህብረተሠብ መፍጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለው አማራጭ የወንጀል ፍትህ አስተዳደርን መዘርጋት ነው፡፡ ይህ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር እንዲኖር ህግ አውጭ፣ ህግ ተርጓሚና አስፈፃሚ አካላት መኖር አለባቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ህግ አውጪው እንደ ወንጀል አድርጐ የሚቆጥራቸው ድርጊቶች እና ተገቢ ብሎ ያመነባቸውን ቅጣቶች ዘርዝሮ በህግ ያወጣል፤ ህግ ተርጓሚው ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተከሰሱ ሠዎችን ሲቀርቡለት ማስረጃውን አዳምጦ ተገቢውን ውሣኔ ይሰጣል፡፡ አስፈፃሚው አካል በፖሊስ አማካኝነት ወንጀል እንዳይፈፀም ይከላከላል ተፈፅሞም ከሆነ ተጠርጣሪዎች ይዞ ለፍርድ ያቀርባል፡፡ ዓቃቤ ህግ መንግስትን በመወከል ክስ ያቀርባል፡፡ ማረሚያ ቤቶች ቅጣት የተወሰነባቸውን ጥፋተኞች ተቀብለው ያሰራሉ ሌሎች ቅጣቶችም ተወስነው ከሆነ ያስፈፅማሉ፡፡
ስለሆነም የወንጀል ህግና የወንጀል የፍትህ አስተዳደር መሠረታዊ አላማዎች የወንጀል አይነቶችን አስቀድሞ በማሣወቅ የአንድ ህብረተሠብ አባላት ይህንን አውቀው ከጥፋት እንዲታቀቡ ማድረግና ይህን ማስጠንቀቂያ በማይከተሉ ላይ ቅጣት መፈፀም ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የወንጀል ህግ የተለያዩ የህብረተሠብ አባላት ማለትም ሰዎች ከሠዎች ወይም ከቡድኖች ወይም ከመንግስት ጋር ያላው ግንኙነት ይወስናል፡፡ በህግ እውቅና በተሠጠው ግንኙነት መሠረት ድርጊታቸውን ማስተካከል የሚችሉ ህጉ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ሲሆን ይህን ማድረግ የማይቻላቻው በህጉ መሠረት ይዳኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሰውን አላማ ለማሣካት በተለያዩ ጊዜያት የወንጀል ህጐች ድንግጋ በተግባር ላይ አውላለች፡፡ በ1923 ዓ.ም የተደነገገው ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ የዋለው የወንጀል ህግ ነው፡፡ 1949 ዓ.ም የወጣው ደግሞ ሁለተኛውና ከ40 ዓመት በላይ በስራ ላይ የነበረ የወንጀል ህግ ነው፡፡ በየመሃሉም ተጨማሪና ያለውን ከፍተት ሊሞሉ የሚችሉ ህጐች በስራ ላይ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ህግ ከ1949 ዓ.ም ጀሞሮ በስራ ላይ የነበረውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በመተካት ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ. ም ጀምሮ በተግባር ላይ ውሏል፡፡ በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 52(5) ላይ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሠረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣ ነው፡፡ ይህ የወንጀል ህግ ህብረተሠቡን በጉዳት ለመጠበቅ የወጣና እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ድርጊቶችና ለነዚህ የተከለከሉ ድርጊቶች ተገቢ ተብለው የተዘረዘሩ ቅጣቶችን የሚዘረዝር ህግ ነው፡፡ ስለሆነም ቅጣት እና ወንጀል ሁለቱ የወንጀል ህግ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ወንጀል ምን ማለት ነው?

ወንጀል ምን ምን አይነት ባህሪያትን ያካትታል ብሎ ቋሚና አለም አቀፋዊ ትርጉም ለመስጠት ያስቸግራል፡፡ ወንጀል የሚባሉት ባህሪያት ከማህበረሠብ ማህበረሰብ ይለያያሉ፡፡ ማህበረሠቡ ሲያድግ ይለወጣሉ፡፡ ስለሆነም በዛሬ ጊዜ ወንጀል ተብሎ የተደነገገ ድርጊት ወይም ያለማድረግ ከዚህ በፊት ወንጀል ላይሆን ይችላል፡፡ ወይም ከዚህ በፊት ወንጀል ተብሎ የተደነገገ ጉዳይ ዛሬ ወንጀል ላይሆን ይችላል፡፡
የወንጀል ህግ ህግ እና ቅጣቶቹ በአብዛኛው የአለማችን ሃገሮች በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሣሣይነት ቢኖራቸውም በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ልዩነት ሊፈጠር የሚችለው የተለያዩ ሃገሮች ህዝቦች በተወሰኑ ጉዳዮች ያላቸው የአመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ይህ ልዩነት ሃይማኖት ከባህል በስልጣኔ እድገት በሰው ልጆች መብት አጠባበቅ ብለው አስተሣሠብ ሊመነጨ ይችላል፡፡ በዚሁም መሠረት የአልኮል መጠጦችን ማዘዋወር፣ ዝሙት አዳሪዎች፣ ግብረሰዶም፣ ፅንስ ማስወረድ የመሣሠሉት ድርጊቶች በአንዳንድ ሃገሮች የወንጀል ድርጌት ተብለው ክልከላ ተደርጐባቸው ግርፋት ወይም የሞት ቅጣት የመሣሠሉትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች ግን ይሄንኑ ተመሣሣይ ድርጊቶች ያልተከተሉ ወይንም በወንጀል ህግ የማያስጠይቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሆኖም ግን በሠፊው ተቀባይነት ያገኘው ትርጉም የሚከተለውን ይመስላል
ወንጀል ማለት ፡- በወንጀል ህግ የተከለከሉ ድትጊቶችን መፈፀም ወይም እንዲፈፀሙ ትዕዛዝ ወይም ግዴታ የተጣለበቸውን ድርጊቶች አለመፈፀም ነው፡፡
በዚህ መሠረት የወንጀል ህጉ ኃላፊነትን የማያስከትል ተግባር የፈፀሙ ሠዎች በወንጀል እንዳይጠቁ ማድረጊያና ወንጀል የፈፀሙ ቢሆንም እንኳን በህጉ ላይ ከተመለከተው ቅጣት ውጪ በዘፈቀደና ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንግድ እንዳይቀጡ መከላከያ መሣራያ ነው፡፡
የወንጀል ህግ አላማና ግብ

የወንጀል ህጉ አንቀፅ 1 ሁለት ፓራግራፎች ያሉት ሲሆን በመጀመሪያው አላማውን ሲገልፅ ሁለተኛው ግቡን ያብራራል፡፡
አንቀፅ 1
የወንጀል ሕግ ዓላማ፣ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡
የወንጀል ሕግ ግብ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና፣ ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፅሙ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው በማድረግ ነው፡፡


የወንጀል ህግ አላማ

የወንጀል ህግ አላማ ከፍ ብሎ በተቀመጠው አንቀፅ 1 የመጀመሪያው ፓራግራፍ እንደተመለከተው የሃገሪቱ መንግስት፣ የህዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም ደህንነት ስርዓት መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው ይላል፡፡ ይህ ህጉ በመጨረሻ ሊደረስበት ያስበውን አላማ ያመለክታል ስለዚህም የወንጀል ህጉ አላማ አጠቃላይ ህብረተሠቡን ከወንጀል ድርጊቶች መጠበቅና ሰላምን ማረጋገጥ ነው፡፡
በአንቀፁ የተገለፀው “ህዝቦች” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ህገ መንግስቱ ለብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከፍተኛ ጥበቃ ያደረገላቸው በመሆኑ የወንጀል ህጉ ይህንን ሊያንፀባርቅና ህጉ ነዋሪዎቹ በግለሰብነታቸው ብቻ ሣይሆን በልዩ ልዩ ህብረት በተቋቋሙበት ሁኔታ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው፡፡ በተጨማሪም ዜጐቹንም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የውጭ ሃገር ሰዎች ስለሚያጠቃልልና ወንጀል ህግ ጥብቃ የሚያደርገው ለሰዎች ሁሉ ስለሆነ “ዜጐች” ተብሎ በቅድሞው ህግ ተገልፆ የነበረው ነዋሪዎች በሚለው ተተክቷል፡፡
የወንጀል ህጉ አላማ የነዋሪዎቹን ሰላም ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ በግልፅ የሚያመለክተው ከግለሰቦች መብት ይልቅ የህዝቦች መብት ቅድሚያ እንደተሠጠው ነው፡፡ ስለሆነም አንድ የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም በህብረተሠቡ አጠቃላይ ጥቅም ላይ ጉዳት ደርሷል ተብሎ ይገመታል፡፡ በዚህም መሠረት የህዝብ ስርዓት ፣ ሰላምና ፀጥታ ሊጠበቅ የሚችለው የግለሰቦች መብት ሲጠበቅ በመሆኑ በእነዚህ መብቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በህዝብ ጥቅም ወይም መብት ላይ እንደተፈፀመ ወንጀል ይቆጠራል፡፡