Get Mystery Box with random crypto!

#ሀ) በሸሪዓና በፍትሐብሔር ህጉ መሰረታዊ የፖሊሲ ሐሳብ ልዩነቶች የሸሪዓም ሆነ የፍትሐብሔር ህጉ | Tsegaye Demeke - Lawyer

#ሀ) በሸሪዓና በፍትሐብሔር ህጉ መሰረታዊ የፖሊሲ ሐሳብ ልዩነቶች የሸሪዓም ሆነ የፍትሐብሔር ህጉ የውርስ ደንቦች መሰረታዊ ግብ የሟችን ውርስ ለወራሾቹ ማስተላለፍ ቢሆኑም በይዘታቸው አንድ አንድ መሰረታዊ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ይህም ልዩነት ሁለቱ ህግጋት መካከል የተካተቱ የፖሊሲ ሀሳብ ልዩነት ነፀብራቅ ነው፡፡ ከልዩነቶቹ ጥቂቶቹን ስንመለከት፣
የፍትሐብሔር ሕጉ የሟች ወራሾች ከሟች በሀይማኖትና በእምነት መለየታቸው የወራሽነት መብታቸውን አያሳጣቸውም፡፡ በሌላ በኩል ሟች ሙስሊም ከሆነ የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ያልሆኑ ወራሻቹ በሟች ውርስ እንዳይሳተፉ የሸሪዓ የውርስ ደንቦች ይከለክላሉ፡፡
የፍትሐብሔር ህጉ የሟች ሴትና ወንድ ወራሾች በጾታቸው ምክንያት የተለያየ ድርሻ እንዲወስዱ አያስገድድም፡፡ በእኩል የዝምድና ደረጃ እስካላቸው ድረስ እኩል ድርሻ ያገኛሉ፡፡ በሸሪዓ የሟች ሴት ልጆች ከሟች ውርስ አንድ ሶስተኛ የሚሰጣቸው ሲሆን ወንዶች ሁለት ሶስተኛ ይወስዳሉ፡፡
በሸሪዓ ሚስት ባሏን የመውረስ መብት ያላትና ከባሏ ውርስ አንድ ስምንተኛ የማግኘት መብት ያላት ሲሆን በፍትሐብሔር ህግ መሰረት ሚስት ባሏን የመውረስ መብት የላትም፡፡
የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ህግ ሟች ከወራሾቹ አንዱን በኑዛዜ የመንቀል መብት ያለው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን በሸሪዓ ሟች ወራሾቹን በኑዛዜ የመንቀል መብት የለውም፡፡
በፍትሐብሔር ህጉ ሟች በኑዛዜ ንብረቱን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ መብት ያለው ሲሆን በሸሪዓ አንድ ሰው በኑዛዜ ሊያስተላልፍ የሚችለው የንብረቱን አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው፡፡

#ለ) በአፈፃፀም የሚታዩ ችግሮች
በሁለቱ ህጐች መካከል ያሉት እነዚህ እና ሌሎች መሰረታዊ ልዩነቶች ሟች ሙስሊም በሆነ ጊዜና የሟች ወራሾች የሌላ ኃይማኖት ተከታይ ወይም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ በሆኑ ጊዜ ወይም ሟች በጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታና ነጠላ የኑዛዜ ስጦታ ንብረቱን ባከፋፈለ ጊዜ በሸሪአ ተጠቃሚ የሚሆኑት ወራሾቹ በሸሪዓ መሠረት ውርሱ እንዲፈፀም ሌሎች ደግሞ በፍትሐብሔር ህጉ መሰረት ታይቶ እንዲወሰን በየበኩላቸው የወራሽነት ማረጋገጫ ለማግኘትና ውርሱን ለመካፈል ክስ የሚያቀርቡበትና የአንድ ሰው ውርስ ጎን በጎን በሁለት ፍርድ ቤቶች የሚታይበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 34 ንዑስ አንቀፅ 5 ይህንን ችግር ዘለቄታ መፍትሔ ለመስጠት ታስቦ የተደነገገ ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር አዋጅ ቁጥር 188/1992 ታውጇል፡፡ በተለያዩ ክልሎችም የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጆች ታውጀዋል፡፡ እነዚህ የህግ ማዕቀፎች ከመውጣታቸው በፊት የነበሩ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እንዲረዱ የሚስተባበል ባይሆንም አሁንም ቢሆን፣
በህግ ማዕቀፎቹ ድንጋጌዎች ግልፅ አለመሆንና በአንድ አንድ ጉዳዮች ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ የተነሳና
መደበኛው ፍርድ ቤት እና የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ህግን በመተርጎምና በማስፈፀም ሒደት የየራሳቸው ችግር ያለባቸው በመሆኑ
ሁለቱን የውርስ ህግጋት በማስፈፀም በኩል በርካታ ችግሮች እንደሚፈጠሩና ችግሮቹ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አልፈው የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመነጋገሪያ አጀንዳ እየሆኑ መሆኑን አንድ አንድ ጉዳዮችን አንስቶ ማየት ይቻላል፡፡


በአጠቃላይ በአገራችን እየተሰራባቸው ያሉ በርካታ ባህላዊና ኃይማኖታዊ የአወራረስ ሥርዓቶች ከፍትሐብሔር ህጉ የአወራረስ ደንቦች ጋር ጎን በጎን ሥራ ላይ በሚውሉበት ጊዜ የሚከሰቱትን ችግሮች መሰረታዊ ባህሪ ችግሮቹ የሚፈቱበትን የህግ አግባብ በመረዳት ለተግባራዊ እንቅስቃሴ ዝግጁ ለመሆን ስልጠናዎች በአካባቢያችን ያሉትን ባህላዊ ኃይማኖታዊ የአወራረስ ሥርዓቶች መሰረታዊ ደንቦች እና የአፈፃፀም ሥርዓት ላይ ስልጣኖቹ በየአካባቢያቸው የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በጥናቱ ግኝት ላይ የጋራ ውይይት እንዲያደርጉ ማድረግ የላቀ ጠቀሜታ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ ነው፡፡

በአሁኑ ግዜ በተጨባጭ ቢያንስ ሁለት ዓይነት የአወራረስ ስርአት (መደበኛና ሸሪዓ) በመኖሩ አንዳንድ ግዜ አንድ ጉዳይ በሁለቱም ስርአቶች የሚስተናገድበትና ግጭት የሚፈጠርበት ሁኔታ ይከሰታል። የሽሪዓ ፍርድ ቤቶችን ስልጣን የሚሰጠው አዋጅ ክፍተት ያለበት መሆኑን ከላይ ተመልክተናል። በመሆኑም ህጉ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ተሻሽሎ ሊወጣ ይገባዋል። ህጉ እስኪሻሻል ግን የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ምንግዜም ግጭት ሊከሰት የሚችል መሆኑን በጠረጠሩ ጊዜ ጉዳዩን የማጣራትና በተከራካሪ ወገኖች መካከል ፈቃድ በሌለ ግዜ ጉዳዩን ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት የመምራት ሃላፊነት ይኖርባቸዋል።