Get Mystery Box with random crypto!

የሚጣፍጥ ስቃይ ተከታታይ ልብወለድ በያኔት ማስረሻ ክፍል ፵፱ @yanetmasra | Christian Mezmur - ክርስቲያን መዝሙር

የሚጣፍጥ ስቃይ

ተከታታይ ልብወለድ
በያኔት ማስረሻ
ክፍል ፵፱
@yanetmasra

እንደምንም እያልን ኑሮአችንን ለመግፋት እና ለማሻሻል ሞከርን ግን ያሰብነውን ያህል ሊሆን አልቻለም ስለዚህ ጋራዥ ውስጥ ለመስራት ወይም ምግብ ቤት ውስጥ ለማስተናገድ ብቻ ሻል ያለ ገቢ የሚገኝበትን ስራ ለመስራት ማፈላለግ ጀመርኩ ። ብዙ የሚረዳኝ ሰው ስለማላውቅ ስራውን የምፈልገው አንዳንድ ቀን ትምህርት በመቅረት ነው በሄድኩባቸው ቦታዎች ስራ እንደምፈልግ እና እንዲሰጡኝ እጠይቃቸዋለሁ አንዳንዶች ተጨማሪ ሠው እንደማይፈልጉ እና ያሏቸው ሰራተኞች በቂ መሆናቸውን ይገልፁልኛል ። ሌሎች ደሞ እየቀለድኩ የሚመስላቸው ለቀልድ ጊዜ የለንም ብለው ያሰናብቱኛል በዚህ መሀልም አርፈህ ትምህርትህን ብትማር ይሻልሀል የሚሉኝም አልጠፉም ለነዚህ ሠዎች መማር ሳልፈልግ ሳይሆን መማር ሳልችል ቀርቼ መሆኑን ማን በነገረልኝ ብዬ ሳላስብ የቀረሁበት ቀን የለም ። ታድያ ይሄን በማደርግበት ሰአት ማንም ሊያውቅና ሊጠረጥር አልቻለም ፤ በዚህ መልኩ ጥቂት ቀናት ካሳለፍኩ በሗላ እየቆየ ሲሄድ በሱፈቃድ ነገረ ስራዬ ሁሉ አልዋጥልህ አለው አብረን አንድ ትምህርት ቤት ስለምንማር ስራውን ለመፈለግ ያሰብኩ ቀን እንደምቸኩል ነግሬው እንዲሁም ስንለቀቅም አትጠብቀኝ ብዬው እሄዳለሁ ከጊዜ በሗላ ያመጣሁት ፀባይ ጥርጥሬ ውስጥ ከተተው በዛ ላይ በተደጋጋሚ የትምህርት ቤት ጊቢ ውስጥም ፈልጎ ሳያገኘኝ ቀርቷል ምንም ያህል ትምህርት ቤት አለመግባቴን እንዳያውቅ ብጥርም አንድ ነገር እንዳለ ሳይገባው አልቀረም ። ከዛን በሗላ ግን የምለውን ከማመን ይልቅ እኔን ላለማስከፋት ሲል ብቻ " እሺ " ይለኛል እንጂ ፊቱ ላይ ያለማመን ስሜት አነብበታለሁ የማደርገው ባጣ እንጂ መዋሸት በጣም ከባድ እና የራስ ማንነትን ዝቅ የሚያደርግ በእግዚአብሔር ዘንድም የሚጠላ ቢሆንም "የቸገረው እርጉዝ ያገባል " እንደሚባለው ሌላ የመፍትሄ ቁልፍ የሆነ መንገድ በማጣቴ አይናቸውን እያየሁ ዋሸሗቸው



እንደውም አንዳንድ ቀን እቤት ስንሆን እቴቴ " አሁን የምጡ ማብቅያ ተቃርቧል ሁለታችሁም በርትታችሁ አጥንታችሁ ያመጣችሁት ውጤት የምታዩበት የዘራችሁትን የምታጭዱበት ምዕራፍ ላይ ናችሁ ደሞ አምናለሁ መልካም እና ጥሩ ውጤትን አምጥታችሁ ለራሳችሁ ተስፋ ለኛ ደስታ እንደምትሰጡን ስለዚህ በቀረው ጊዜያችሁ በርቱ አምላካችን እግዚአብሔር ከናንተ ጋር ይሁን የምታነቡትን ይግለጥላችሁ " ትለናለች ከእናታዊ ፍቅሯ የተነሳ ይህንን እንደምትለን ባውቅም የኔ አካሄድ ግን ከዛ ተቃራኒ ስለነበር ምርቃቷ እና ምክሯ ፍርሀትን ይለቅብኛል ዝም ላለማለት ብቻ " አሜን " እያልኩ በሱፈቃድን አጅበዋለሁ

  አንድ ቀን እንደተለመደው ስራ ፍለጋ ከላይ እታች ስዳክር ውዬ እድል ቀናኝ ካፌ ውስጥ ገብቼ ለባለቤቱ ስራ እንደምፈልግ ስነግራቸው በአባታዊ አስተያየት እየተመለከቱኝ " እውነት ስራ ብሰጥህ ትሰራለህ ማለቴ ትችላለህ "  አሉኝ " በሚገባ በደንብ እሰራዋለሁ ስራ ለማግኘት ምን ያህል እንደደከምኩ ስለማያውቁ ነው ብቻ አምነው ይቅጠሩኝ " አልኩና ቢያዝኑልኝ እና ቢቀጥሩኝ ብዬ የቤተሰቤን የድህነት ሁኔታ ዝክዝክ አድርጌ ነገርኳለው ታድያ ሳላስበው እንባዬም በመውረዱ ንግግሬን አደመቀው ። " እሺ እዚህ ካፌ ውስጥ ፅዳት እንድታፀዳ እና የሚሰሩትን በማየት በማይኖሩበት ጊዜ አስተናጋጆቹን እንድታግዝ እቀጥርሀለሁ ፤ ማወቅ ያለብህ ነገር ማጭበርበር  ፣ እና ስርቆት ምን ያህል እንደምጠላ ነው በአግባቡ ስራህን ከሰራህ ቋሚ አስተናጋጅ ሆነህ ትሰራለህ " አሉኝ በደስታ ጮቤ ረገጥኩ ቶሎ  ሀሳባቸውን ሳይቀይሩ ብዬ በማሰብ " ታድያ አሁን ልጀምር ? " አልኳቸው " አይ ነገ ትጀምራለህ በጠዋት ናና ልጆቹ መስራት ያለብህን ያሳዩሀል " አሉኝ ትልቅ ምስጋናን አቅርቤላቸው ወደ ቤቴ ሄድኩ....ይቀጥላል
#share


     ይ ላ ሉን
@christian_mezmur
@christian_mezmur