Get Mystery Box with random crypto!

በመ/ር ገብረ መድኅን እንየው ቀኖናን በመጣስ ሹመት ቢፈጸምስ??ሁለተኛ ክፍል የሐዲስ ኪዳን ክህነት | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

በመ/ር ገብረ መድኅን እንየው
ቀኖናን በመጣስ ሹመት ቢፈጸምስ??ሁለተኛ ክፍል
የሐዲስ ኪዳን ክህነት  ባሕርየ ቃል ባሕርየ ሥጋን በተዓቅቦ ቢዋሐድ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ለቃል ሆነ ። ንጉሠ ነገሥት ሊቀ ካህናት ተባለ ። የባሕርይ መሥዋዕትነቱን  ራሱ ሠዋዒ ተሠዋዒ ሁኖ  ለራሱ አቀረበ ።ክርስቶስ ነቅዐ ክህነት ወሀቤ ሀብት ነውና በእግርም በግብርም ለተከተሉት አባቶቻችን ሐዋርያት  ከምንጩ በጸጋ ሥልጣነ ክህነትን ተቀበሉ። በዕለተ ዕርገት  ሐዋርያትን እየባረካቸው አፈፍ አለ፣ በድረግ አለ ፣ የርቀት ያይደለ የርህቀት ተሠወራቸው።
ሐዋርያትም የተቀበሉትን ክህነት ለመጻኢው ትውልድ የሚገባውን እየለዩ በአንብሮተ እድ አቀብለዋል።ወደእኛም ከሐዋርያት ወደ ቅዱስ ማርቆስ ከማርቆስ ወደ አቡነ ባስልዮስ ኢትዮጵያዊ ከዚያም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዘመናችን ደርሷል።ያለምንም ተመትሮ በቅብብሎሽ የሚሰጡ :-

1.ሐዋርያዊ ክህነት፦ብዙ ጳጳሳት ፣ካህናት ቢኖሩም ብዙ ክህነት የለም።

2.ሐዋርያዊ ትምህርት፦12ሐዋርያት ቢኖሩንም ብዙ የሐዋርያነት ተልእኮ የለም።

3.ሐዋርያዊ አረዳድ፦ብዙ የሚረዱ ቢኖሩም ግላዊ መረዳት የለም።

4.ሐዋርያዊ ልጅነት፦ብዙ ልጆች ቢኖሩም ብዙ ልጅነት የለም።

5.ሐዋርያዊ አምልኮ፦ብዙ አምላኪዎች ቢኖሩም ብዙ ተመላኪ የለም ያው አንዱ ነው እንጁ።

6.ሐዋርያዊ ዕለተ ዓርብ፦ብዙ ዓርቦች ቢኖሩም ብዙ ዕለተ ስቅለት የለም አንዲቷ ሐዲስ ዕለት ናት።

7.ሐዋርያዊት እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ...ናቸው። እነዚህ በቅብብሎሽ የሌሉት ሰው ኦርቶዶክሳዊ ሊባል አይችልም። አባቶቻችን ሐዋርያት የክህነት ቀኖናን በሠሩበት አንቀጽ ሹመትን በውግዘት የሚከለክሉ ዋና ዋናዎች፦

√_ሲሞናዊነት(በእጅ መንሻ መሾም) √_መለካዋነት(በንጉሥ ግዳጅ መሾም)
√_በቃሁ ነቃሁ ብሎ በራስ መሾም...ፈጽሞ በውግዘት የተከለከለ ነው።

የሐዋርያት ቀኖና በውግዘት እና ያለ ውግዘት የተሠራ ቀኖና ነው።በውግዘት የተሠራውን ቀኖና እስከ ዕለተ ምጽአት እንጠብቀዋለን እንጂ አንለውጠውም። ያለውግዘት የሠሩት ግን ብያኔያዊ ነውና ቦታውን ሁኔታውን አይተው  ሊያሻሽሉት ይችላሉ። ለምሳሌ፦ምእመናን አሥራት በኩራታቸውን ይስጡ ይላል። ድርቅ ቢሆን፣ስደት ቢሆን በመሳሰለው ዘመን ተቸግረው ሳለ ባይሰጡ ዘእንበለ ግዘት ነው። ውግዘት የለውም  ይላል ፍት.ነገ አን.5።
ክህነትን በተመለከተ ግን ፦አምላካችን "ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?"የማቴ6፥27 ያለውን ማለትም ከእናንተ በቃሁ ነቃሁ ብሎ ለራሱ ሥልጣነ ክህነትን ገንዘብ ማድረግ የሚቻለው የለም እንዳለ። የግድ ሹሙኝ ብሎ የሚሾም የለም።በሹመት ምክንያት አስፈራርቶ ቢሾም ከምእመናን አንድነት የተወገዘ ነው። ወይም በንጉሥ አስፈራርቶ ሹመትን የሚሻት እና የሚሾም የተወገዘ ነው ይለናል ።ከዚህ ቀኖና ጋር እንዴት ነው የምንታረቀው? በአራተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ  ንጉሡ ያለውን የግድ ተቀበሉ ሲባል አባታችን ቅዱስ ዲይስቆሮስ የሰማያዊ ንጉሥ ሕግ እያለ የምድራዊ ንጉሥ ኑፋቄን አልቀበልም ቢል ጽህሙን ነጭተው ጥርሱን አርግፈው አባረውታል

ዛሬ ጠቅላዩ ብለዋልና ይፈጸም ይሾሙ የሚባል ከሆነ የዲዮስቆሮስ ሃይማኖት አለች ማለት ይቻላልን? የጠቅላዩ ሥራ ሀገር መምራት እንጂ ቀኖና ማፍረስ  አይደለም።ይሄ ቀኖና ተጥሶ ሹመቱ ቢፈጸም ከሐዋርያት አንድነት ጉባኤ እየተለየን እንደሆነ መታወቅ አለበት። ቤተ ክርስቲያንም ወደማያባራ የቀኖና ንትርክ መግባቷ አይቀርም። በዚህ መካከል የሚጠፋውን ምእመን መገመት አያዳግትም። ይህ መለካዊ ሹመት ተፈጽሞ መነሻ የሌለው ስብራት ከሐዋርያት ተለይተን  ከምንሰበር በእነሱ ምክንያት የሚመጣውን ሰማዕትነት እንደ ሻሸመኔ ክርስቲያኖች ብንቀበል ይሻላል።
አሁን በመንበሩ ላይ ያላችሁ አባቶቻችንም እናከብራችኋለን እንወዳችኋለን። ግን ታሪክ ይቅር ወደማይለው የቤተ ክርስቲያን መከራ እጃችሁን እንዳታነሡ በልጅነት መንፈስ እንጠይቃለን።
መሾም ካስፈለገ በትሩፋታቸው የሚያጸድቁ በትምህርታቸው የሚያስታርቁ አባቶችን መርጦ መሾም የተገባ ነው። ያም ቢሆን በቅድሚያ ከሰማይ ከዋክብት የበዛ ችግራችንን አስተካክለን ሹመት ቢፈጸም ያማረ ይሆን ነበር።
  ።                      
ይሄንን ዝም ብንል ቀኖና ሐዋርያት ይዋቀሰናል መስሎ ለመኖር ስንል የሐዋርያትን ፣ የሠለስቱ ምዕት ዓለም አቀፋዊ ጉባኤያዊ ቀኖና ባላየ ባልሰማ ማለፍ አንችልም። ቀኖናው ይጠበቅ መለካዊ ሹመት ይቁም።

"ወለእመ ተራድአ በመኳንንተ ዝንቱ ዓለም ወተሰይመ ለቤተ ክርስቲያን እምኀቤሆሙ ይትመተር ፦#የዚህን ዓለም መኳንንት ረዳትነት ይዞ በእነሱ ኃይል በምእመናን ላይ መዓርገ ክህነት የተሾመ ይሻር። ወይሰደድ ውእቱኒ ወኩሎሙ እለተሳተፍዎ ፦#እሱም እሱን በሥራ እሱን የመሰሉት ሰዎችም ይሻሩ። #ገንዘብ ሰጥቶ በንጉሥ አስፈራርቶ የተሾመ እንደ አረማዊ ይቆጠር። #ከምእመናን አንድነትም ይለይ። #ሁለት ጊዜ የተሾመም ይሻር። #ረስጠብ፳፩ #ፍት.ነገአን.፭።   ትእዛዝ ፲፯:- በታወቀ ኃጢአት ምክንያት በትክክል የተሻረ ኤጲስ ቆጶስም ቢኖር ቄስም ቢኖርና ከተሻረ በኋላ ከመሻሩ በፊት በክህነቱ ይሠራ የነበረውን ሥራ ሲሠራ ቢገኝ ፈጽሞ ከቤተክርስቲያን ይራቅ። "

ሥርዓተ ጽዮን ቁጥር ፳፯:- "በታወቀ በደል በትክክል የተሻረ ኤጲስ ቆጶስ ቢኖርና ቀድሞ በተሰጠው ሥልጣን ለመሥራት ቢደፋፈር እስከዘለዓለሙ ድረስ ከቤተክርስቲያን ይሻር።"

አብጥሊስ ፳፯:- "ባደረገው በደል ከቤተክርስቲያን ያስወጡት ኤጲስ ቆጶስ ቢኖር ከተሻረ በኋላ ከመሻሩ በፊት ይሠራው የነበረውን የክህነት ሥራ ሲሠራ ቢገኝ እስከመጨረሻው ከቤተክርስቲያን ይሰናበት።"

ቀሌምንጦስ ቀኖና ፳፯:- "ባደረሰው በደል ምክንያት ሥልጣኑ ተይዞ ከቤተክርስቲያን የተባረረ ኤጲስ ቆጶስ ከተወገዘ በኋላ ውግዘቱን አቃሎ በክህነት ሲያገልግ የተገኘ እስከመጨረሻው ከቤተክርስቲያን ይሰናበት።" ይላል
እነዚህን እና  የመሳሰሉ ሐዋርያዊ  ቀኖናዎች እንዴት ነው የምናልፈው?

"ስንናገር የተሳሳትን የሚመስላችሁ የሳሳትነው ዝም ያልን ጊዜ ነው" መ/ር ኃይለ ማርያም ዘውዱ እንዳሉ ዝም ብንል የጥፋት ተባባሪዎች ነን።