Get Mystery Box with random crypto!

__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፳፪___ አንቀጽ ፴፮ ይህ አንቀጽ መጠመን ማ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፳፪___
አንቀጽ ፴፮
ይህ አንቀጽ መጠመን ማስጠመን (መከራየትና ማከራየት) እንዲገባ ይናገራል። (በእንተ ተዐስቦ ነው)።
፩) ተዐስቦ ረብሕ ጥቅም ለማግኘት በመጠመን በማስጠመን ጊዜ በቃል የሚዋዋሏት ውል ናት። ዋጋው አስጠማኝ በቆረጠው ሊሆን ይገባል።
+
፪:- የመጠመን የማስጠመን ሥርዓት በተጠማኝ በአስጠማኝ ፈቃድ እንጂ ያለእነዚህ ፈቃድ አይጸናም አይፈጸምም። አስጠማኝ ለተጠማኝ ከብቱን መሬቱን አሳይቶ አስታውቆ መስጠት ይገባዋል። በሥራም ቢሆን መጠመን ይገባል። ይኽውም ልብስ ለመስፋት ከብት ለመጫን መጠመን ነው።
+
፫:- መጻሕፍት መምህራን የከለከሉትን መጠመን ማስጠመን አይገባም።
+
፬:- ልብስ ለሚሰፋ ለሚያጥብ፣ ለእንጀራ ጋጋሪ፣ እነዚህን ለመሰሉት ሁሉ ሥራቸውን ሳይፈጽሙ ዋጋቸውን ስጡን ማለት አይገባም። ሥራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ቢሆን ነው እንጂ።
+
፭:- ባለቦታ በዋጋዋ ከተዋዋለ በኋላ ቢያድሩም ባያድሩም ከተዋዋላቸው ሰዎች የቦዘኑበትንም ያደሩበትንም የማደሪያ ዋጋ ይቀበል።
+
፮:- ሠራተኛ ሁሉ ዋጋውን እስኪቀበል ድረስ የሚሠራውን መያዝ ይገባዋል። (ሐተታ) ቀለም አግቢ ልብሱን፣ አንጥረኛ ጻሕሉን መያዝ ይገባዋል።
+
፯:- ማናቸውንም የተጠመነ ሰው በእርሱ እጅ ሳለ ቢጠፋ፣ ጥፋቱ በተንኮል በቸልታ ካልሆነ መክፈል አይገባውም።
+
፰:- በዓለ ሐመር ከባልንጀሮቹ ተለይቶ አክብዶ ቢጭን፣ ነፋስ ማዕበል ሞገድ በተነሣበት ጊዜ በሰባራ በአሮጌ መርከብ ጭኖ ቢያሰጥም መክፈል ይገባዋል። ቸል ባይል ግን መክፈል አይገባውም።
+
፱:- ለልብስ አጣቢ ከሰጡት ልብስ አይጥ ቢበላበት መክፈል ይገባዋል።
+
፲:- ተጠማኙን ጥፋት ክፋት እንዲያገኘው እያወቀ ማናቸውንም ገንዘብ ያስጠመነ ሰው ባይነግረው መክፈል ይገባዋል። ዘንዶ እባብ ያለበት ፈት ቦታ እንደማስጠመን ያለ ነው።
+
፲፩:- ቤትን ለውሽባ ቤትነት መጠመን ማስጠመን አይገባም። ዘር ለመዝራት መሬት መጠመን ማስጠመን ይገባል።
+
፲፪:- እስከዚህ ቦታ እሄዳለሁ ብሎ ከብት የተጠመነ ሰው አልፎ የሄደ ቢሆን ብትጠፋ መክፈል ባትጠፋ አልፎ የሄደበትን ጨምሮ መስጠት ይገባዋል።
+
፲፫:- ቦታ የተጠመነ የገዛ ሰው ቢኖር ለማደር የማያበቃ ነውር ቢያገኝበት ውሉን ማፍረስ ይገባዋል።
+
፲፬:- አናጢ ሥራውን ከፈጸመ በኋላ ዋጋውን መቀበል ይገባዋል።
+
አንቀጽ ፴፯
ይህ አንቀጽ የሁሉ መሄጃ የአውራ ጎዳናውን፣ የሁሉ መውጫ መጋጫ ሜዳውን፣ ቤት የመሥራትን ነገር፣ በእርሻና በእርሻ መካከል የሚሄድ የውሃን ጎዳና ነገር ይናገራል።
፩) የአንድነት ቤት ካላቸው ሰዎች አንዱ ከባልንጀሮቹ ፈቃድ ወጥቶ ጠባቂ ሹም መሾም አይገባውም። የአንድነቱንም አጥር ቅጥር አንዱ ማፍረስ ወይም መሥራት አይገባውም። በባልንጀራው ፈቃድ ቢሆን ነው እንጂ።
+
፪) አንድ ሰውስ እንኳ በአንድነቱ አጥር አጠገብ የማድ ቤት፣ የውሽባ ቤት መሥራት አይገባውም።
+
፫) አንድ ሰው በደርብ ያሉትን ሰዎች የሚያፍናቸው ጢስ የሚወጣበት ማድ ቤት የውሽባ ቤት ቢሠራ ጢስ ከማጤስ ይከልከል። በደርብ ያሉትም ምድር ቤት ያሉትን እንዳያሳዝኗቸው እጣቢውን ማፍሰስ ጥራጊውን መጣል አይገባቸውም።
+
፬) ሰው ሁሉ በቤቱ ጎረቤቱ የሚያዝንበትን ሥራ መሥራት አይገባውም።
+
፭) አንድ ሰው ቅጽር ሊሠራ ቢወድ ከባልንጀራው አንድ እርምጃ ርቆ ይሥራ። ቤት ቢሆን ስድስት እርምጃ ርቆ ይሥራ። የውሃ ጉድጓድ ቢሆን አምስት ክንድ ይሁን። (ይህ በዘመናቸው የነበረ ሲሆን በአሁን ዘመን ላይሠራ ይችላል። ምክንያቱም የቤት አሠራሩ የቀድሞውና የአሁኑ የተለያየ ነውና)
+
፮:- ዳኞች የተወሰነውን መመርመር ይገባቸዋል። ወጉን ታሪኩን ማጥናት መመርመር ይገባቸዋል። ቃል ለቃል ሲያያዝ የመጣውን፣ ከልማደ ሀገር የተገኘውን ማወቅ መመርመር ይገባቸዋል።
+
፯:- ቅጽሩ ወደጎዳና አዘንብሎ ሰዎች አፍርስልን ብለውት ሳያፈርስ ቀርቶ ተንዶ ሰው ቢጎዳ ባለቤቱ መክፈል ይገባዋል።
+
አንቀጽ ፴፱
ይህ አንቀጽ የተአምኖን ነገር ይናገራል።
፩) ራሱን የቻለ አካለ መጠን ያደረሰ ሰው በእውነት በደሉን ቢናገር ኃጢአት ስለሠራ ንስሓ ይገባዋል። ገንዘብ ሰርቄያለሁ ቀምቻለሁ ቢል ገንዘብ መክፈል ይገባዋል።
+
፪:- ብድሩን የሚከፍለውን ያጣ ድኃ አለብኝ ቢል ይጸናል። ያን ጊዜ መክፈል አይገባውም። ሲያገኝ ይክፈል እንጂ።
+
፫:- አንድ ሰው ለጽንስ ከርስቱ ቢያዝለት፣ ገንዘብ ጽፎም ቢያዝለት ሕያው ሆኖ ከተወለደ ይጸናለታል።
+
አንቀጽ ፵
ይህ አንቀጽ ጠፍቶ ስለተገኘ ገንዘብ ይናገራል።
፩:- ለወንድምህ የጠፋውን ገንዘብ መልስለት። ምንም ቅርብህ ባይሆን ሰውየውንም ባታውቀው ወደቤትህ አግባው። ወንድምህ አምጣ እስኪልህ ድረስ በአንተ እጅ ይቀመጣል። ካገኘህበት ቦታ ወስደህ ሰባት ቀን መልኩን ዓይነቱን ሳይናገር ገንዘብ የጠፋው ይበል። ዓይነቱን በትክክል ተናግሮ ባለቤቱ የእኔ ነው ቢል ያገኘው ሰው በዳኛ ፊት ይመልስለት።
+
፪:- በጠፋበት ጊዜ ባለቤቱ ያልታወቀለት ገንዘብ ያገኘ ሰው፣ ባለቤቱን የሚያውቅ ቢመጣና ምልክቱን የሚናገር ቢመጣ፣ የእርሱ እንደሆነ የልቡናውን ጥርጥር ቢያርቅለት ገንዘቡ እንደመሆኑ ይመልስለት። ያለዚያ ግን ገንዘቡ ጥቂት ቢሆን መብላት መጠጣት ይገባዋል።
+
፫:- ገንዘብ ያገኘ ሰው ገንዘቡ ከተገኘበት ሀገር ካሉ ሰዎች ወገን ባይሆን በዳኛ እጅ በዳኛ እጅ ያኑረው። ሊያስመረምርም ቢወድ እንደወደደ ያድርግ። ከምርምሩ ቀን በኋላ አንድ ሰው መጥቶ የጠፋው ገንዘብ የእርሱ እንደሆነ ቢናገር፣ ገንዘቡ ባገኘው ሰው እጅ ቢኖር ይመልስለት። ቢሸጠውም ዋጋውን ይመልስለት። ቢበላው ባለጸጋ ቢሆን መሰሉን መክፈል ይገባዋል። ድኃ ቢሆን የተረፈውን መመለስ ይገባዋል። ከገንዘቡ ባይተርፍ ግን ምንም ምን ክፈል አይበሉት።